ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማ አባ ጅፋር

ከነገ ጨዋታዎች መካከል ዘግየት ብሎ የሚጀምረው የቡና እና አባ ጅፋር ጨዋታ የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን የመጨረሻ ትኩረት ነው።  

የወቅቱ የሊጉ መሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያ ቡናዎች ቻምፒዮኑ ጅማ አባ ጅፋርን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም 10፡00 ላይ ይጀምራል። በ22 ነጥቦች አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሳምንቱ አጋማሽ መቐለ ላይ 1-0 ተሸንፈው ተመልሰዋል። የነገ ተጋጣሚያቸው አባ ጅፋርን ጨምሮ በርካታ ተከታዮቻቸው ተስተካካይ ጨዋታዎች ያሏቸው በመሆኑም በመደበኛዎቹ መርሐ ግብሮቻቸው ተጨማሪ ነጥቦችን መጣል መሪነታቸውን እንዳያሳጣቸው ያሰጋል። ሆኖም አብዛኛዎቹን ነጥቦቻቸውን ወደሰበሰቡበት ሜዳቸው መመለሳቸው ለኢትዮጵያ ቡናዎች በመልካምነት የሚነሳ ጉዳይ ነው። ከአፍሪካ ውድድሮች ውጪ የሆነው ጅማ አባ ጅፋር ፊቱን ወደ ሊጉ በመለሰበት ጨዋታ ወላይታ ድቻን 2-0 መርታት ችሏል። ቡድኑ ከአምስት ተስተካካይ ጨዋታዎቹ ውጪ ያሉትን መደበኛ ጨዋታዎች በማሸነፍ ከቀጠለ የአምናውን ታሪክ ለመድገም ወደሚያስችለው መንገድ መምጣት ይችላል።

ኢትዮጵያ ቡና ቶማስ ስምረቱ ፣ ሱለይማን ሎክዋ እና ሚኪያስ መኮንን በጉዳት ሳቢያ የምያጣ ሲሆን ልምምድ የጀመረው አስራት ቱንጆም ወደ ጨዋታ አይመለስም። በጅማ አባ ጅፋር በኩል አዲስ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ዘሪሁን ታደለ እና ኤልያስ አታሮ ብቻ ወደ አዲስ አበባ በመጣው ስብስብ ውስጥ አልተካተቱም።

አማኑኤል ዮሃንስ የተመለሰለት ኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍሉ ጥንካሬ በተለይም በመከላከሉ ረገድ ከፍ እንዳለ መናገር ይቻላል። ሆኖም በማጥቃት ሂደት ውስጥ ያለበትን ክፍተት ቀርፎ መቅረብ በእጅጉ ያስፈልገዋል። ቡና የመስመር ተመላላሾችን እንደማሰለፉ የሜዳውን ስፋት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል የአማካይ ክፍል ጥምረት ያስፈልገዋል። ይህ እንዲሆንም በነገው ጨዋታ የካሉሻ አልሀሰንን ትክክለኛ ሚና ማግኘት ከአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የሚጠበቅ ይሆናል። ጅማ አባ ጅፋር በጨዋታው በቀጥተኛ አቀራረብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ ይገመታል። ከመስመር አጥቂዎቹ ወደ ውስጥ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረትም ከጠንካራው የተጋጣሙው የመከላከል አደረጃጀት ጋር መፋለም ይጠበቅበታል። የማማዱ ሲዲቤ ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ መምጣትም ጅማዎች በግብ ፊት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የሚያስችል አዕምሯዊ ጥንካሬ እንዲኖራቸው የሚረዳ ይሆናል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጅማ አባ ጅፋር ወደ ሊጉ በመጣበት ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በተገናኘባቸው ጨዋታዎች አልተሸነፈም። የመጀመሪያው በጅማ 2-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ በአዲስ አበባው ጨዋታ ደግሞ ያለግብ ተለያይተዋል።

– አዲስ አበባ ላይ ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ያላገኛቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች አምስቱን በድል አጠናቀዋል። ከሸገር ደርቢ ውጪም በሁሉም ጨዋታዎች ግብ አስቆጥረዋል።

– ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን ከሜዳው ውጪ አምስት ጨዋታዎችን ሲያደርግ አንዴ ድል ሲቀናው ሁለቴ በአቻ ሁለቴ ደግሞ በሽንፈት ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ መሪነት ይካሄዳል። ለሚ እስካሁን በመራባቸው ሦስት ጨዋታዎች ስምንት የቢጫ ካርዶችን ሲሰጥ እና አንድ የፍፁም

ቅጣት ምት ውሳኔም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (3-4-2-1)

ዋቴንጋ ኢስማ

ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ወንድይፍራው ጌታሁን

አህመድ ረሺድ –  ዳንኤል ደምሴ – አማኑኤል ዮሃንስ – እያሱ ታምሩ

ካሉሻ አልሀሰን – ሳምሶን ጥላሁን

አቡበከር ናስር

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3) 

ዳንኤል አጄዬ

ዐወት ገብረሚካኤል – ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ተስፋዬ መላኩ

ይሁን እንዳሻው – አክሊሉ ዋለልኝ – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *