የአሰልጣኞች አስተያየት | ደደቢት 0-1 ስሑል ሽረ 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መቐለ ላይ ከተደረገው የደደቢት እና ስሑል ሽረ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 
“በዛሬው ውጤት የደጋፊዎቻችን ድርሻ ትልቅ ነበር” ገብረኪሮስ አማረ – ስሑል ሽረ

ስለ ጨዋታው 

ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ደርቢ እንደ መሆኑ ከበድ ይላል ብለን ጠብቀን ነበር። እንደገመትነውም ከባድ ነበር። የግድ ማሸነፍ እንዳለብን አምነን ነበር የገባነው። ከእረፍት በፊት በነበረ እንቅስቃሴ ይዘነው የገባነው አጨዋወት ፍሬ ባያፈራም ጥሩ ጎኖች ነበሩበት። ከእረፍት በኃላ ግን ወርደን ነበር፤ ውጤቱ ግን ጥሩ ነው።

ከዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ክለቡ ስለ መመለሳቸው

በ2008 ቡድኑን ወደ ከፍተኛ ሊግ ያሳደኩት እኔ ነበርኩ። በዛም ሰዓት በአቅሜ ጥሩ ስራዎች ሰርቼያለው። በዚ ዓመት ደሞ እስካሁን ማሸነፍ አልቻልንም ነበር። ይሄ የመጀመርያ ሶስት ነጥባችን ነው። በጣም ነው ደስ ያለኝ። ይሄ ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው ከሚመለከታቸው አካላት ተጋግዘን እንሰራለን። በዛሬው ውጤት የደጋፊዎቻችን ድርሻ ትልቅ ነበር። በጣም አመሰግናለው፤ ለነሱ ትልቅ ክብር ነው አለኝ።

ስለ ቀጣይ ጨዋታቸው 

ቀጣይ ጨዋታችን ከወልዋሎ ጋር በሜዳችን እናሸንፋለንም ብዬ አስባለው። በርግጥ የተለየ ዝግጅት አናደርግበትም። ጨዋታው በሜዳችን እንደመሆኑ ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብዬ አስባለው።


” ችግር ባሉብን ላይ እየሰራን ለቀጣይ ጨዋታዎች እንዘጋጃለን” ኤልያስ ኢብራሂም 

ስለ ጨዋታው 

ከዕረፍት በፊት ተቀዛቅዘን ነበር፤ የተቃራኒ ቡድን አጨዋወትም ከራሳቸው ሜዳ ቶሎ ለመውጣት እና ፈጣን አጥቂዎቻቸው ተጠቅመው ረጃጅም ኳሶች ነበር የሞከሩት። እኛ ደሞ ያንን አክሽፈን ወደ ራሳችን እንቅስቃሴ ለመግባት ነው ስንጥር የነበረው ኳሱን ይዘን ለመጫወት ያ አልሆነም። ከዕረፍት በኋላ ደሞ የነበሩብንን ክፍተቶች በደምብ በማየት የተጫዋቾች ለውጥ አድርገን ጨዋታው ለመቆጣጠር ሞክረናል አጋማሹ ከተጀመረ በኃላም የግብ ዕድሎች ፈጥረን መጠቀም አልቻልንም። በየጨዋታው ተመሳሳይ ስህተቶች ነው እየሰራን ያለነው። የትኩረት ማነስ አለ። ዛሬ የተቆጠረብን ግብም በዛ ችግር ነው።

ስለ ቀጣይ የቡድኑ ጉዞ 

የዛሬን ጨዋታ አሸንፈን ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ነበር አቅደን የመጣነው። በተስተካካይ ጨዋታዎች ትኩረት አድርገን  ከነዛ ጨዋታዎች የተወሰኑ ነጥቦች ወስደን ደረጃችን እናሻሽላለን የሚል እቅድ ይዘን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። በዛሬው ጨዋታ ያቀድነው አልሆነልንም። በቀጣይ ያሉብንን ችግሮች አስተካክለን ችግር ባሉብን ላይ እየሰራን ለቀጣይ ጨዋታዎች እንዘጋጃለን።

ዛሬ ቡድኑ የሚታወቅበትን ኳስ ቁጥጥር ብልጫ አለማሳየቱ

ባለፉት ጨዋታዎች ቡድናችን ጥሩ ቅርፅ ያለው እና ጥሩ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነበር። ክፍተታችን ግብ የማግባት ነበር፤ ዛሬ ግን ተጫዋቾችን ላይ ጉጉት ነበር። ይሄን ጨዋታ የምናሸንፍ ከሆነ ደረጃችን የምናሻሽል መሆናችንን ስለሚያውቁ ጉጉት ነበራቸው። በዛ ምክንያት ነው እንጂ ቡድኑ በእንቅስቃሴ ደረጃ ወደ ጥሩ ብቃት መጥቷል ብዬ ነው የማስበው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *