ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ስሑል ሽረ

ባህርዳር ሽረን በሚያስተናግድበት የነገ ተስተካካይ ጨዋታ ዙሪያ የሚነሱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

የአማራ እና ትግራይ ክለቦች ጉዳይ ፈር ከመያዙ አስቀድሞ ከ2ኛ ሳምንት መርሐግብሮች መካከል በይደር የቆተው የባህር ዳር እና ሽረ ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም ይደረጋል። ከአስረኛው ሳምንት በኋላ ከውጤት የራቀው ባህር ዳር ከወልዋሎ ሽንፈት እና ከአማራ ደርቢ አቻ በኋላም ሁለት ተከታታይ የ 1-1 ውጤቶችን አስመዝግቧል። 13ኛ የሊግ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ባለሜዳዎቹ በዚህ ጨዋታ ካሉበት 9ኛ ደረጃ በጥቂቱ ከፍ ማለት ሲችሉ ወደ መልካም አጀማመራቸው ለመመለስ እንደሚፋለሙ ይጠበቃል። 13ኛው ሳምንት ላይ ደደቢትን በማሸነፍ የመጀመሪያ የሊግ ድላቸውን ያሳኩት ሽረዎች በተቃራኒው ሳምንት በሜዳቸው መጀመሪያውን ሽንፈት ገጥሟቸዋል። የዛሬውን የመከላከያን ድል ተከትሎም ዳግም ወደ ወራጅ ቀጣና የገቡ ሲሆን በዚህ ጨዋታ ቦታውን ለወላይታ ድቻ አስረክበው ከፍ ማለትን ይልማሉ። 

ባህር ዳር ከተማ ሙሉ ስብስቡን በመያዝ ሲሆን ጨዋታውን የሚያደርገው በ10ኛው ሳምንት ደደቢትን ባሸነፈበት ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አማካኙ ዳንኤል ኃይሉ ከጉዳቱ በማገገሙ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ይካተታል ተብሎ ይጠበቃል። የእንግዳዎቹ ሽረዎች ስብስብ ውስጥም በተመሳሳይ የተሰማ የጉዳት እና ቅጣት ዜና የለም። 

ሁለቱም ቡድኖች ለኳስ ቁጥጥር ቦታ የሚሰጡ በመሆነቸው ጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። ከጅማው ጨዋታ በተለየ የመስመር አጥቂዎቻቸውን የመከላከል ተሳትፎ በመቀነስ ለፊት አጥቂው ቀርበው እንዲጫወቱ ሊያደርጉ ይሚችሉት ባህር ዳሮች መሀል ላይ ኳስ ቢይዙም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ከደረሱ በኋላ ወደ መስመሮች እንደሚያመዝኑ ይጠበቃል። ከሜዳም ውጪ አጥቅቶ የመጫወት ባህሪ የሚያሳዩት ሽረዎች አማካይ ክፍል ላይ ካላቸው የቁጥር ብልጫ አንፃር የኳስ ቁጥጥሩን የበላይነት መውሰድ ከቻሉ ወደ ልደቱ ለማ የሚያደርሷቸው ኳሶች ዋነኛ የጥቃት ምንጮቻቸው ሊሆኑ ይችላሉ። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጨዋታው ለሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ የእርስ በርስ ግንኙነታቸው ይሆናል፡፡
– ባህር ዳር ከተማ ሜዳው ላይ ካስተናገዳቸው አምስት ክለቦች ሁለቱን አሸንፎ ከሦስቱ ጋር ነጥብ ተጋርቷል።
– ስሑል ሽረዎች ከሜዳቸው በወጡባቸው የመጀመሪያ ሦሰት ጨዋታች ሽንፈት ሲደርስባቸው በመጨራሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን አራት ነጥቦችን አሳክተዋል፡፡

ዳኛ

– 10ኛው ሳምንት ላይ ባህርዳር እና ደደቢትን ዳኝቶ የነበረው ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በአምስት ጨዋታዎች ላይ ዳኝቶ 24 የማስጠነቂያ እና አንድ የቀይ ካርዶችን የመዘዘ ሲሆን ምንም የፍፁም ቅጣት ምት አልሰጠም።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሐሪሰን ሄሱ

ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ  – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ

ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት – ግርማ ዲሳሳ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት  – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ሙሉጌታ ዓንዶም

ክብሮም ብርሀነ – ደሳለኝ ደባሽ

አሸናፊ እንዳለ – ሳሙኤል ተስፋዬ – ሸዊት ዮሃንስ

ልደቱ ለማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *