ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ አዳማ ከተማ

ከመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች መካከል አንዱ በሆነው የባህር ዳር እና አዳማ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች ልናነሳ ወደናል።

በሳምንቱ አጋማሽ ተስተካካይ ጨዋታዎችን ያደረጉት ባህር ዳር እና አዳማ በነጥብ እኩል ሆነው በ15ኛ ሳምንት መርሐግብር ነገ 09፡00 ላይ በባህርዳር ይገናኛሉ። ከሦስት ትከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ሽረን መርታት የቻሉት ባህር ዳሮች አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እያላቸው ወደ ድል በመመለስ በ21 ነጥቦች ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ በማለት እያራቁ ወደነበሩበት የዋንጫ ፉክክር መቅረብ ችለዋል። ጨዋታው ባህር ዳር ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረበት ሆኖም አልፏል። በሜዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግደው የነበሩት አዳማ ከተማዎች ደግሞ ከወልዋሎው ድል በኋላ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል። ከስምተኛው እስከ አስረኛው ሳምንት በተከታታይ ድሎች ያሳዩት መነቃቃት በመቀዛቀዙም ሁሉንም ጨዋታዎች አድርገው ከ7ኛ ደረጃ ማለፍ አልቻሉም።

ባህር ዳር ከተማ ያለምንም የጉዳት እና ቅጣት ሙሉ ስብስቡን በመያዝ ለጨዋታው ሲደርስ በአዳማ በኩል ግን አምስት ተጫዋቾች ጨዋታው ያልፋቸዋል። በጊዮርጊሱ ጨዋታ በጡንቻ መሸማቀቅ ተቀይሮ የወጣው ተስፋዬ በቀለ ፣ አንዳርጋቸው ይልሀቅ እና ሱለይማን መሀመድ በጉዳት ቡልቻ ሹራ ደግሞ በቅጣት ምክንያት ሲሆን ወደ ባህር ዳር ያላመሩት ልምምድ የጀመረው ሱራፌል ጌታቸውም ለነገው ጨዋታ አይደርስም።

ከሜዳው ውጪ የሚጫወተው አዳማ ከተማ የውድድሩ አጋማሽ የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያደርግ በመሆኑ ሙሉ ነጥብ ለማግኘት ያለመ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ሆኖም የቡልቻ ሹራ አለመኖር ይበልጥ ያዳከመው የቡድኑ የማጥቃት ሂደት የከንዓን ጥሩ ዕይታ እንዲሁም የበረከት እና ዳዋ ፍጥነት ላይ ብቻ ተመስርቶ ተገማችነት እየታየበት መሆኑ ጠንካራውን የባህር ዳር የኋላ ክፍል አልፎ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዳይቸገር ያሰጋዋል። ኳስን ተቆጣጥረው ተጭነው የመጫወት ዕቅድ እንደሚኖራቸው የሚጠበቁት ባህር ዳሮች በበኩላቸው የአዳማ የመስመር ተከላካይ ቦታዎች በጉዳት ምክንያት ለውጦችን ማስተናገዳቸው የማይቀር በመሆኑ ለፈጣኑ የመስመር ጥቃታቸው ጥሩ አጋጣሚ የሚሆንላቸው ይመስላል። ከዚህ ባለፈ በሽረው ጨዋታ ቡድኑ ከተሻጋሪ ኳሶች ግቦችን ማግኘቱ አካሄዱን እንደ ተጨማሪ የግብ ዕድል መፍጠሪያ አማራጭ ሊጠቀምበት እንደሚችል የሚጠቁም ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እርስ በርስ የሚገናኙበትን ጨዋታ ያደርጋሉ።

– ባህር ዳር ከተማ እስካሁን ስድስት ክለቦችን ያስተናገደ ሲሆን ከዕኩሌታው ጋር ነጥብ ሲጋራ ዕኩሌታውን ደግሞ ማሸነፍ ችሏል። በዚህም በሜዳው ምንም ሽንፈት አላገኘውም።

– ከሜዳቸው ውጪ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፉት አዳማዎች ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተው ሲመለሱ ሁለት ጊዜ ደገሞ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።

ዳኛ

– በሦስት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በመዳኘት ስድስት የቢጫ ካርዶችን እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምትን የሰጠው ብርሀኑ መኩሪያ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሐሪሰን ሄሱ

ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳግማዊ ሙሉጌታ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ

ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት – ግርማ ዲሳሳ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱራፌል ዳንኤል – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱለይማን ሰሚድ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ

ኤፍሬም ዘካርያስ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *