የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 2-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሚከተለውን አስያየት ሰጥተዋል።

“በዋናነት የዛሬው ድል የኛ ሳይሆን የደጋፊው ድል ነው” ደለለኝ ደቻታ – ወላይታ ድቻ

” በቅድሚያ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን። የድሉን 75% ደጋፊው ይወስዳል፡፡ የደጋፊው አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር፡፡ ዛሬ ማሸነፋችን ደስ ብሎኛል። የጊዮርጊስን አጨዋወት ከዚህ በፊት በተወሰነ መልኩ ተመልክተናል፡፡ በሶስት ተከላካይ ነው የሚጫወቱት። ሁለት አማካዮቻቸው በረጅሙ ይጫወታሉ። ዳር እና ዳር ላይ ደግሞ ክፍተት አለ፡፡ ያንን ክፍተት ለመጠቀም ነበር ያለምነው። የገቡትም ኳሶች በነኚህ ቦታዎች የመጡ ናቸው፡፡ ሰርተን ስለነበር ጨዋታው አልከበደንም፡፡ ከዚህ በፊት ተከላካዮቻችን ስህተት ይሰሩ ነበር፡፡ ያ ዛሬ ላይ ሙሉ ለሙሉ ቀርፈዋል የሚል እሞነት አለኝ። በዋናነት የዛሬው ድል የኛ ሳይሆን የደጋፊው ድል ነው፡፡

“ዛሬ ሁሉም ነገር የተሳሳተ ነበር” ስቴዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

” ሜዳው እጅግ መጥፎ ነበር፤ በሊጉ መጥፎው ሜዳ ይህ ነው። ዳኛውም ጥሩ አልነበረም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እኛ ጥሩ አልነበርንም። ይህ ነበር ትልቁ ችግር። የኛ እንቅስቃሴ ከተጋጣሚያችን ተነሳሽነት እና የታጋይነት መንፈስ ጋር የሚመጣጠን አልነበረም። የጨዋታ እቅድ ይዘን ገብተናል፤ ግን አልተገብረነውም። ኳስ ለመቀባበል አስበን ነበር፤ ነገር ግን አልቻልንም። ረጅም ኳስ፣ አጭር ኳስ እንዲሁም የማዕዘን ምቶች እና የእጅ ውርወራ ሳይቀር በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም። ዛሬ ሁሉም ነገር የተሳሳተ ነበር። በ15 ጨዋታዎች መጥፎውን አቋም ያሳየነው ዛሬ ነው። በጣም ተበሳጭቻለሁ፤ እዚህ ድረስ ሊደግፉን የመጡ ደጋፊቻችንንም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ።

ከዛሬው ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማስመዝገብ አይገባንም። በጨዋታው አንድም ኢላማ የጠበቀ ሙከራ አላደረግንም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *