ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ስሑል ሽረ

ከዛሬ የሊጉ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የፋሲል እና ሽረን ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችንን እንሆ…

የዓመቱ 14ኛ ጨዋታውን የሚያደርገው ፋሲል ከነማ ዛሬ 09፡00 ላይ በአፄ ፋሲለደስ ስታድየም የመጀመሪያ ዙር ጉዞውን የሚያገባድደው ስሑል ሽረን ያስተናግዳል። ጨዋታው ለፋሲል ከነማም ጎንደር ላይ የሚደረግ የዙር የመጨረሻ ጨዋታ ነው።

ከመቐለ ጋር በነበረው ተስተካካይ ጨዋታ ሽንፈት የገጠመው ፋሲል ከነማ በስሌት ደረጃ በሊጉ አናት ላይ ለመቀመጥ የነበረው ተስፋ በእጅጉ ጠቧል። ቡድኑ ከዚያ ቀደምም በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ከመጋራት ባለፈ ድል አለማስመዝገቡም ጭምር ነው ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ እንዲንሸራተት ያደረገው። ያም ቢሆን በሁለተኛው ዙር በፉክክሩ ውስጥ በጥንካሬ ለመዝለቅ ከቀሩት ሁለት ጨዋታዎች በተለይም በሜዳው ከሚያደርገው የዛሬው ጨዋታ የሚያገኛቸው ነጥቦች ወሳኝ ናቸው። 

በባህር ዳር ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት መልስ ወደ ጎንደር የተሻገሩት ስሑል ሽረዎች ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፉበት በሚገኙበት ሊግ የወራጅ ቀጠና ሳይርቁ የውድድሩን አጋማሽ ለማገባደድ ተቃርበዋል። አሰልጣኞቻቸውን ካሰናበቱ በኋላ በደደቢት ላይ ያሳኩትን ድል መድገም ባለመቻላቸውም 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን በመጠኑም ቢሆን ከአደጋው ዞን የነጥብ ልዩነት ለመፍጠር ዛሬ ከአፄ ፋሲለደስ ስታድየም በድል የመመለስ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

ሙጂብ ቃሲም ከጉዳት ያልተመለሰለት ፋሲል ከነማ ልምምድ የጀመሩት ዮሴፍ ዳሙዬ እና ፋሲል አስማማውም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱለት ሲሆን ወሳኝ አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው ግን ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት መልስ ቡድኑን ያገለግላል። በስሑል ሽረ በኩል ደግሞ ሠለሞን ገብረመድህን እና ኢብራሂም ፎፎና በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ የሀፍቶም ቢሰጠኝ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በ2009 ሊጉን የተቀላቀለው ፋሲል ከነማ ሽረን የሚያስተናግድበት ይህ ጨዋታ የቡድኖቹ የመጀመሪያ የሉጉ ግንኙነታቸው ይሆናል።

– ከአምና ጀምሮ ላለፉት ስምንት ጨዋታዎች ከሽንፈት የራቀ ውጤት ያላቸው ፋሲል ከነማዎች ዘንድሮ ጎንደር ላይ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች  ሦስቱን በድል ሲያጠናቅቁ በቀሪዎቹ ሦስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋተጋርተዋል።

–  ስሐል ሽረ ከሜዳው ውጪ አምስት ጨዋታዎችን ሲያደርግ የመጀመሪያዎቹን ሦስቱን በሽንፈት ሲደመድም ከመከላከያ ነጥብ በመጋራት ደደቢትን ደግሞ ማሸነፍ ችሏል። 

ዳኛ

– ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ አዲስ አበባ ላይ የድቻ እና ሲዳማን ጨዋታ የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዚህ ጨዋታ ላይ ተመድቧል። ቴዎድሮስ በአምስት ጨዋታዎች 15 የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ     

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ኤፍሬም ዓለሙ – ሐብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

አብዱርሀማን ሙባረክ – ኢዙ አዙካ –  ሽመክት ጉግሳ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት  – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ሙሉጌታ ዓንዶም

ሳሙኤል ተስፋዬ – ደሳለኝ ደባሽ

አሸናፊ እንዳለ – ጅላሉ ሻፊ – ሸዊት ዮሃንስ

ልደቱ ለማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *