ሪፖርት | ደቡብ ፖሊስ በጅማ አባጅፋር ላይ ግማሽ ደርዘን ጎሎች በማስቆጠር ተከታታይ ድሉን አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር የመጨረሻ በሆነው መርሐ ግብር ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ጅማ አባጅፋን አስተናግዶ ግማሽ ደርዘን ጎል በማስቆጠር 6-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ደቡብ ፖሊሶች ኢትዮጵያ ቡናን በአዲስ አበባ ስታዲየም 2-1 ከረቱበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በኃይሉ ወገኔና አዳሙ መሐመድን አስወጥተው ሄኖክ አየለ እና አበባው ቡታቆን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲያካትቱ በተስካካይ ጨዋታ ከድሬዳዋ ጋር በሁለት የግብ ልዩነት ከመመራት ተነስቶ ነጥብ በተጋራው አባጅፋር በኩል የሶስት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ሚኪያስ ጌቱ በዘሪሁን ታደለ፣ ከድር ኸይረዲን በመላኩ ወልዴ፣ ኤልያስ ማሞ በሄኖክ ገምቴሳ ተተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡


የደቡብ ፖሊስ ፍፁም የሆነ የእንቅስቃሴ እና የግብ ማግባት ብልጫ በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ በ30 ደቂቃዎች ውስጥ ባስቆጠሯቸው ግቦች ጨዋታውን ጨርሰው የወጡበትን ድል ነው ያስመዘገቡት። በተለይ በቀኝ እና በግራ የተሰለፉት የተሻ ግዛው እና በረከት ይስሀቅ እጅጉን ተዳክሞ ለታየው የጅማ አባጅፋር የመስመር ተከላካይ በእጅጉ ፈታኝ ሆነው ውለዋል። 4ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ ወደ ጅማ የግብ ክልል ባደላ መልኩ የተገኘችዋን ኳስ ብሩክ አየለ በተከላካዮች መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጠውን የተሻ ግዛው የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደግብነት በመለወጥ ነበር ቢጫ ለባሾቹ ገና በጊዜ ቀዳሚ መሆን የቻሉት፡፡


ከዚህች ግብ በኋላ ጅማዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ፖሊስ የግብ ክልል ደርሰው ዲዲዬ ለብሪ ሲያሻማ መስዑድ መሐመድ በግንባሩ ከገጫት ኳስ ውጪ ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ሙከራን ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ ፖሊሶች የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ሄኖክ፣ የተሻ፣ በረከት፣ ብሩክ እና ዘላለም በሜዳው ቁመትም ሆነ ስፋት በቅብብል የጅማ አባጅፋር የግብ በር ቶሎ ቶሎ በመድረስ ፋታ ማሳጣት የቻሉ ሲሆን ከ13ኛው ደቂቃ ጀምሮም ለቀጣዮቹ 17 ደቂቃዎች ተከታታይ 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

በ13ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲገባ በረከት ይስሀቅ ተቀብሎ ከብሩክ ጋር በጥሩ ቅብብል ያሻገረውን ኳስ ዘላለም ኢሳይያስ አስቆጥሮ የደቡብ ፖሊስ ወደ 2-0 መሪነት እንዲሸጋገር አድርጓል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ብሩክ አየለ ያመቻቸለትን ግሩም ኳስ ተጠቅሞ የተሻ ግዛው ለራሱ ሁለተኛ ለፖሊስ ሶስተኛ ግብን ከመረብ አሳርፏል፡፡ በ18ኛው ደቂቃ ብሩክ አየለ በረጅሙ የሰጠውን ኳስ ሄኖክ አየለ ተቆጣጥሯት ከሳጥኑ ውጪ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብን አስቆጥሮ የግብ መጠኑን ወደ አራት ማሳደግ ችሏል፡፡ 28ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ይስሀቅ ከግራ ጠርዝ ወደ ግቡ የላካትን ኳስ ሄኖክ አየለ ደርሶባት አምስተኛውን ግብ ካስቆጠረ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ዛሬ በማቀበሉ ረገድ ተሳክቶለት የዋለው በረከት ይስሀቅ ያሻገረውን ዘላለም ኢሳይያስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ስድስተኛ ግብ በማስቆጠር ደቡብ ፖሊስ 6-0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡


ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ አጨዋወትን ስንመለከት ጅማዎች ከነበራቸው ደካማ የአርባ አምስት ደቂቃ ቆይታ ተነቃቅነው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም፤ ግብ ለማስቆጠር ያለመ ቅያሪ በማድረግ አማካዩ አክሊሉ ዋለልኝን በአጥቂው ቢስማርክ አፒያ፣ ዲዲዬ ለብሪን በቴዎድሮስ ታደሰ ቢተኩም የደቡብ ፖሊስን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት ተቸግረው ታይተዋል፡፡ በአንፃሩ ደቡብ ፖሊሶች ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ተከላካዮቻቸው ከግብ ክልላቸው ሳይርቁ እንዲጫወቱ በማድረግ እና በሚገኙ አጋጣሚዎች ወደፊት በመሄድ ተጨማሪ ግብን ለማስቆጠር ጥረትን ያደረጉበት ነበር፡፡

50ኛው ደቂቃ የአበባው ቡታቆ እና ግብ ጠባቂው ሐብቴ ከድርን ያለመናበብ ተመልክቶ ማማዱ ሲዲቤ ያገኛትን ዕድል መጠቀም ሳይችል ከድር ቀድሞ የያዘበት ተጠቃሽ የጅማ አጋጣሚ ሲሆን 76ኛው ደቂቃ ላይ አናጋው ባደግ በማማዱ ሲዲቤ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ግርማ በአግባቡ በመጠቀም አባጅፋርን ያልታደገች ግብ  አስቆጥሯል፡፡


ግብ ከተቆጠረ በኋላ ባሉት ደቂቃዎች ጅማዎች ውጤቱን ለማጥበብ በሙሉ የማጥቃት ኃይል እንደሚጫወቱ ቢጠበቅም ተጠቃሽ የግብ እድል መፍጠር ተስኗቸዋል። ይልቁንም ፖሊሶች በመጠናቀቂያ አምስት ደቂቃዎች ብልጫን ወስደው በመጫወት 85ኛው ደቂቃ ላይ የተሻ ግዛው ኤልያስ አታሮን አልፎ በቀኝ በኩል ወደ ውስጥ ገብቶ የላካት ኳስን ፊት ለፊት ከግቡ ጋር ብሩክ ኤልያስን ያገናኘች ብትሆንም ብሩክ ግልፅ አጋጣሚዋን መጠቀም ሳይችል አምልጣዋለች፡፡ በተጨማሪም ተቀይሮ የገባው ብሩክ ኤልያስ አክርሮ መትቶ ዘሪሁን የያዘበት ይጠቀሳል። ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማ ጥሩ የግንባር ኳስን ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ጨዋታው ፖሊሶች ከእረፍት በፊት ባስቆጠሯቸው ግማሽ ደርዘን ግቦች ታግዘው 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ተከታታይ ሁለተኛ ሙሉ ነጥባቸውን አግኝተዋል።


በውጤቱ ባለፉት 13 ጨዋታዎች ካሳካው ነጥብ በላይ በሁለት ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻለው ደቡብ ፖሊስ በ11 ነጥቦች ከ15ኛ ወደ 14ኛ ከፍ ብለዋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የደቡብ ፖሊስ ደጋፊዎች አሰልጣኝ አላዛር በዋና አሰልጣኝነት መቀጠል አለበት፤ አዲስ አሰልጣኝ አንፈልግም በማለት በገብረክርስቶስ ቢራራ ሹመት ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *