ሪፖርት | የሱራፌል ዳኛቸው ማራኪ ጎሎች ፋሲልን ወደ ድል መልሰውታል

በ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ጎንደር ዐፄ ፋሲል ስቴዲየም ስሑል ሽረን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 3-0 በመርታት ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።

ፋሲል ከነማ ወደ መቐለ አቅንቶ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከተመለሰው ስብስቡ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። ሰዒድ ሀሰን፣ ኤፍሬም ዓለሙ፣ በዛብህ መለዮ እና ኢዙ አዙካን ሲያሳርፍ ሰለሞን ሐብቴ፣ ዓለምብርሀን ይግዛው፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ኤዲ ቤንጃሚን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ አካትቷል። በአንፃሩ ስሑል ሽረ በተስተካካይ ጨዋታ ከአራት ቀን በፊት በባህርዳር ከተማ 2 – 0 ከተረታበት ስብስቡ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ግብጠባቂው ሐፍቶም ቢሰጠኝ ፣ ሙሉጌታ አምዶም እና ሰዒድ ሁሴን አሳርፎ ሰንደይ ሮቲሚ ፣ ነፃነት ገብረመድኅን እና ልደቱ ለማን በመተካት ወደ ሜዳ ገብቷል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመኪና አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡት የፋሲል ከነማ ሁለት ደጋፊዎች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። የጎንደር ከተማ ከንቲባም ለፌዴሬሽኑ ለስራ አስፈፃሚ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የምስጋና ስጦታ በማበርከት ነበር የጨዋታው ጅማሬ የሆነው።

ነፃ እና ማራኪ የጨዋታ ፍሰት የተመለከትንበት፣ ግሩም ጎሎች የተስተናገዱበት፣ ጠንካራ የጎል እድሎች የተፈጠሩበት፣ ከጥሩ የዳኝነት አመራር ጋር የታየበት ጨዋታ የአንድ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ብልጫ የተመለከትንበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

ዐፄዎቹ በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ መጣላቸው ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ፈልገው እንደገቡ በሚያሳይ ሁኔታ የዳኛው የጨዋታ ጅማሬ ፊሽካ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ በፍጥነት ነበር ወደ ጎል በመድረስ አደጋ መፍጠር የጀመሩት። 5ኛው ደቂቃ አብዱራህማን ሙባረክ ሳይጠበቅ ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት አጥብቆ የመታውን በዕለቱ ስራ በዝቶ በዋለበት የሽረ ግብጠባቂ ሰንደይ እንደምንም ወደ ውጭ አውጥቶታል። የመጀመርያ የግብ ዕድል በአብዱራህማን አማካኝነት የጀመሩት ባለ ሜዳዎቹ ፋሲሎች ብዙም ሳይቆይ 7ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ሰለሞን ሀብቴ ጎል መሆን የሚችል ዕድልን ኳሱን በግንባሩ ከመሬት ጋር አንጥሮ ለጥቂት መቶት ወጥቶበታል።

ድንቅ የውድድር ጊዜ በአዲሱ ክለቡ ፋሲል ከነማ ጋር እያሳለፈ የሚገኘው እና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነፃ የጨዋታ ሚና ተሰቶት በሁሉም የሜዳ ክፍል በመገኘት የቡድኑን አጨዋወት ፍጥነት በመጨመር እና ኳሶችን በማደራጀት ለቡድን አጋሮቹ በመበተን የዛሬው ጨዋታ ኮከብ የነበረው ወጣቱ የመስመር አጥቂ ሱራፌል ዳኛቸው በ10ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከሽረ ተከላካዮች ጋር ታግሎ ለመምታት ሲሞክር ወደ ኋላ የተመለሰውን ኳስ አየር ላይ እያለ ከሳጥን ውጭ እጅግ ግሩም ጎል በማስቆጠር ዐፄዎችን መሪ አድርጓል። ጎሉም በስቴዲየም የነበረውንም ደጋፊዎችን ደስታቸውን የተለየ እንዲሆን አድርጓቸዋል።

በዚህ ሁሉ ሂደት ኳሱን በአግባቡ መቆጣጠር የተሳነባቸው እና ተደጋጋሚ በሚሰሩት ስህተቶች ያልተረጋጉት እንግዶቹ ሽረዎች ሜዳ ውስጥ አልነበሩም ማለት ይቻላል። የሱራፌልን እንቅስቃሴ ማቆም ያልቻሉት ሽረዎች በዐፄዎቹ የሚደርስባቸው ጥቃት ቀጥሎ 14ኛው ደቂቃ ቤንጃሚን ከሱራፌል ዳኛቸው የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎ ወደ ጎል ቢመታውም ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ጠርዝ ሊወጣበት ችሏል። በተመሳሳይ ከመሐል ሜዳ ግራ ጠርዝ ሱራፌል እና ሽመክት በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ፊት ሰብረው የገቡትን ሽመክት በመጨረሻ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ለአጥቂው ኤዲ ቤንጃሚን ሰጥቶት ጎል አስቆጠረ ሲባል ግብጠባቂው ሰንደይ ያዳነበት ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ነበር። በ25ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ዲሜጥሮስ ወ/ሥላሴ በግንባሩ ገጭቶ ራሱ ላይ ጎል ለማስቆጠር ተቃርቦ ኳሱ ለጥቂት የወጣው ኳስም ሌላው ተጠቃሽ የግብ እድል ነበር።

የጨዋታው ፍጥነት ግሎ በፋሲሎች የበላይነት በቀጠለው ጨዋታ 28ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዱራህማን የተሰጠውን ኳስ የመስመር አጥቂው ሽመክት ጉግሳ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ የዐፄዎችን የጎል መጠን አሁንም ከፍ ማድረግ የሚችል ዕድል ሆኖ አልፏል። በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ሱራፌል ዳኛቸው ከመሐል ሜዳ እየገፋ ተጫዋቾችን በማለፍ ከሳጥን ውጭ ኳሱን አመቻችቶ በመምታት ለግብ ጠባቂው የመመለስ እድል በማይሰጥ መልኩ አስደናቂ ጒል አስቆጥሮ የፋሲልን መሪነት አስፍቷል።

አልፎ አልፎ ካልሆነ በቅር እምብዛም ወደ ፊት መጓዝ ያልቻሉት ሽረዎች ከፋሲሎች የሚደርስባቸውን ጫና ተቋቁመው ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ በመሆኑ የመጀመርያው አጋማሽ ላይ የተሳካ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ በጨዋታው ጥሩ ጥምረት ያሳዩት አብዱራህማን፣ ሱራፌል እና ሽመክት በጥሩ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ከገቡ በኋላ ሽመክት ብቻውን በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው አብዱራህማን እሰጣለው ብሎ ያጠረበት ኳስ ሦስተኛ ጎል መሆን የሚችል ሌላ አጋጣሚ ነበር።

ከእረፍት መልስ ጅማሬ በዐፄዎቹ በኩል በተለያዩ ጊዜያት ተቀይሮ በመግባት ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው እና ዛሬ በመጀመርያ ተሰላፊነት በመግባት ዕድል በማግኘት ተስፈኛ ተጫዋች መሆኑን እያሳየ የሚገኘው ዓለምብርሀን ይግዛው 47ኛው ደቂቃ በጥሩ ሁኔታ የፈጠረውን የግብ ዕል የሽረ ግብጠባቂ ሰንደይ አድኖበታል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተደረገው የተጫዋች ቅያሪ ብዙም በጨዋታው ላይ የተለየ ነገር አለመፍጠሩ እና በእንቅስቃሴ ተዳክመው መቅረባቸው እንደ መጀመርያው አጋማሽ ፈጠን ያለ እንቅስቃሴ አላየንበትም። 68ኛው ደቂቃ ዓለምብርሀን ይግዛው በጥሩ ሁኔታ ወደ ፊት የጣለለትን ሽመክት ጉግሳ የግብ ጠባቂውን አቋቋም አይቶ ባጠበበት ቦታ መሬት ለመሬት ቢመታውም የግቡን ቋሚ ታኮ ወጥቶበታል።

በተመሳሳይ ሽመክት ሌላ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ የግብ ጠባቂውን አቋቋም አይቶ ቺፕ አድርጎ ለማስቆጠር ሲሞክር ያሳጠረው ኳስ እና ተቀይሮ የገባውና በትናትናው ዕለት የጋብቻ ስነ ስርዓቱን የፈፀመው ኤፍሬም ዓለሙ 82ኛው ደቂቃ ከአዙካ በቀኝ መስመር የተሰጠውን ኳስ አገባው ሲባል ግብጠባቂው ሰንደይ እንደምንም ተወርውሮ የያዘበት የዐፄዎችን የግብ መጠን ከፍ ማሳደግ የሚችሉ የጎል ዕድሎች ነበሩ።

በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ኤፍሬም ዓለሙ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ጨርሶ ሰጥቶት ተቀይሮ የገባው ኢዙ አዙካ ጎል በማስቆጠር የፋሲሎችን የጎል መጠን ወደ ሦስት አሳድጎታል። በመጨረሻም የጨዋታው መጠናቀቂያ ጥቂት ደቂቃ ውስጥ በተደጋጋሚ ወደ ጎል መድረስ የቻሉት ሽረዎች በተለይ በሄኖክ አማካኝነት የፈጠሩት የጎል እድል በግብ ጠባቂው ጀማል ጣሳው እንደምንም ወደ ውጭ ወጥቶ ጨዋታው በዐፄዎቹ የበላይነት 3-0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *