አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከነገው የአለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ በፊት በቡድናቸው ዝግጅት ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የመግለቻውን ሀሳብ እንዲህ አቅርበዋል፡፡
‹‹ ዝጅግታችንን ከጀመርን 9 ቀን ሆኖናል፡፡ ከውጭ የመጡት ተጫዋቾቻችን ከዚህ በፊት በተናገርነው መሰረት አቅማቸውን ማየት ስለነበረብን እርስ በእርስ በማጫወት አይተናል፡፡ የዋሊድንም አቋም ለማየት ፈልገን ነበር፡፡ በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ቶሎ ባለመምጣቱ መመልከት አልቻልንም፡፡ እርስ በእርስ ማቻወታችን የአዳዲሶቹንም ሆነ የነባሮቹን ብቃት ለማየት ጠቅሞናል፡፡ 26 ተጫዋች ይዘናል፡፡ ወደ 18 ለመቀነስ እና ምርጥ 11 ለመምረጥ ሚዛናዊ መስፈርት ያስፈልጋል፡፡ ታዋቂ ሯጮች ወደ ኦሎምፒክ በስማቸው ብቻ አይሄዱም፡፡ ከዛ በፊት የሚዘጋጁ ውድድሮችን ማሸነፍ አለባቸው፡፡
‹‹ በግጥሚያው ጌታነህን ነበር ማየት የፈለግነው፡፡ ሽመልስ አብሮን ስለነበረን አቅሙን እናውቃለን፡፡ ከዛ ውጪ ጌታነህ ያለፉት 2 ጨዋታዎች አልነበረም፡፡ አሁን ወደ ቡድኑ ሲመለስ ከሌሎች አጥቂዎች ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚለውን አይተናል፡፡ በኛ ግምት ከበፊቱ የተሻለ ነገር አይተናል፡፡ (ካሉን ልጆች አንፃር)
‹‹ ነገ ጠዋት ከልምምድ በኋላ ወደ 18 እንቀንሳለን፡፡ ዛሬ ማታ የሚከሰተውን ስለማናውቅ 21 ተጫዋቾችን ይዘናል፡፡ ረፋድ ላይ 18 ተጫዋች እናሳውቃለን፡፡ ››
ድካም
‹‹ ከፊፋ አባል ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ነች በአጭር ጊዜ ብዙ ውድድር ያደረገችው፡፡ ለዛ ነው ድካም የመጣው፡፡ ተጫዋቾቹ ደግሞ በዚህ ደረጃ መጫወት እስከቻሉ ድረስ ድካምን መቋቋም አለባቸው፡፡ ››
የሜዳ አድቫንቴጅ መጠቀም
‹‹ በህዝባችን ፊት እና በለመድነው አየር ስለምንጫወት አድቫንቴጅ መውሰድ አለብን፡፡ እኛ ከሳኦቶሜ እና ቡሩንዲ ከሜዳ ውጪ ተጫውተን አድቫንቴጅ ይዘን እንደመጣነው እነሱም ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ወደኋላ ሳንል ያለ የሌለ አቅም ተጠቅመን ማሸነፍ አለብን፡፡ ስንሰራ የነበረውና ሜዳ ላይ የምንገባውም ማሸነፍ የሚለውን ይዘን ነው፡፡ የተሻለ አድቫንቴጅ ይዘን ለመሄድ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ ››
እቅድ
‹‹ እቅዳችን ኢንተርናሽናል ጨዋታ በመጫወት ራሳችንን መገምገም ነበር፡፡ ይህ ባለመሳካቱ ከቡና ወይም ጊዮርጊስ ጋር ለመጫወት አቅደን ነበር፡፡ እሱም ባለመሳካቱ ሶስተኛ አማራጭ ወስደናል፡፡ በተመሳሳይ ቦታ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በተቃራኒ አሰልፈን ማን እንደሚሻል አይተናል፡፡ ከመጀመርያው ፕላን የወጣን ቢሆንም ከሚፎካከረው ተጫዋች ጋር ማጋጠሙን ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ቋሚ 11 ውስጥ ለመግባት ሁሉም እድል አለው፡፡ በግጥሚያው አዳዲስ ተጫዋቾች ጫና ምን ማለት እንደሆነም አይተዋል፡፡ ››
ራምኬል ሎክ
‹‹ ራምኬል ከእስር ቤት ተለቆ ሆቴል ነው ያለው፡፡ ነገ ግን አይጫወትም፡፡ አእምሮው ጥሩ ይሆናል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ከመጣበት ሁኔታ አንፃር ለጨዋታ ዝግጁ ይሆናል ብዬ ስለማልጠብቅ አላሰልፈውም፡፡ ወደ ኮንጎ በሚጓዘው ቡድን ውስጥ ግን ይካተታል፡፡ ››
ልምድ
‹‹ ከዚህ በፊት እንዳልነው ከውጪ የሚመጡትን ልምድ ስላላቸው እንጠቀምባቸዋለን ብለን ነበር፡፡ ልምድ ግን ሜዳ ላይ ካልሰራ ወደ ፕላን ቢ እሄዳለን፡፡ ልምዳቸው የምንፈልገውን ነገር ካልሰጠን በቀጥታ ጨዋታ ላይ ከሚገቡ በእርስ በእርስ ጨዋታ ሞክረን ብቁ ከሆኑ እናሰልፋቸዋለን፡፡
‹‹ በፕላን መንቀሳቀስ አለብን፡፡ አንደኛው ፕላን ካልሰራ ወደ ሌላው መሄድ አለብን፡፡ ሁሉም እኩል መብት ተሰጥቶት እንዲወዳደር ማድረግ ነው ሃላፊነቴ፡፡ እድል ባልሰጥ ነበር የኔ ችግር የሚሆነው፡፡ በልምድ በኩል ቡድኑ ውስጥ ስዩም አለ ሽመልስ ፣ ጌታነህ እና ዳዊትም አሉ፡፡ በነሱ ተጠቅመን ቡድኑን እንዲመሩ እናደርጋለን፡፡ ስዩም የአእምሮ ደረጃውን በተግባር ስላሳየ ነው አምበል የሆነው፡፡ ››
ስለ ተጋጣሚያቸው
‹‹ እኛም ኮንጎ በቅርብ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች አይተናል፡፡ (አሰልጣኝ ክሎድ ለርዋ የኢትዮጵያን የቅርብ ጨዋታዎች እንደተመለከቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡) የተመለከትናቸው ጨዋታዎች እንደ መንደርደርያ ይሆኑናል፡፡ የአጨዋወት ዘዴያቸውን ገምግመናል፡፡ ምን ማድረግ እንደሚገባንም ከተጫዋቾቼ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ››
ዋሊድ አታ
‹‹ ዋሊድን በግል ያሰራነው ከቡድኑ ጋር ዘግይቶ በመቀላቀሉ ነው፡፡ ዋሊድ የፕሮፌሽናል ተጫዋች ፀባይ አለው፡፡ ከአውሮፓ ቢመጣም እዚህ ያለው ፀባዩ ከምንጠብቀው በላይ ነው፡፡ ሁልጊዜ አዎንታዊ ነሀገሮችን የሚያስብና ራሱን የማያካብድ ልጅ ነው፡፡ ለዛ ነው ልምምድ ስሰራ አቅለሽልሾኛል ፣ አየሩ ከብዶኛል ብሎ ፊት ለፊት የነገረኝ፡፡ ››