‹‹ የተከሰተው ችግር ሁሉም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በአግባቡ አለመስራታችን ውጤት ነው ›› ዮሴፍ ተስፋዬ

ለኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ውጪ መሆን ምክንያት ናቸው በሚል በፌዴሬሽኑ ከስራቸው የታገዱት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ትላንት በሂልተን ሆቴል በግላቻ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ መግለጫውን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

 

ልጠራ የተገደድኩበት ምክንያት…

-ህግን ያልተከተለ ውሳኔ ስለተላለፈ

-ፌዴሬሽኑ ጠዋት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ አመኔታ የሌላቸውን ወይንም ያልተፈፀሙ ነገሮች ተፈጥረው ስለተነገሩ፡፡

-ህዝቡ እና ሚድያው የእኔን ምላሽ መስማት ስላለበት

-ስለታገድክ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ንግግር ማድረግ አትችልም ተብያለሁ፡፡ እንደዛ ከሆነ በግሌ እጠራለሁ ብያለሁ፡፡ በዚህ መሰረት የነሱን መግለጫ ልጠብቅ ብዬ ነው ቆይቼ በግሌ መግለጫ የሰጠሁት፡፡

-ፌዴሬሽኑም በኔ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መሳተፍ እንደሚችል በህዝብ ግንኙነቱ በኩል አስታውቄያለሁ፡፡

 

በመጀመርያ ደረጃ መላው ህዝብ ፣ የስፖርት ቤተሰቡ እና በተለይ ሴት ተጫዋቾቻችንን እጅግ እጅግ በተሰበረ ልቦና ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

 

ብቃት የለውም ስለመባሉ…

‹‹ በካፍ የሴቶች ኮሚቴ ተወካይ ነኝ፡፡ የሴቶችን ልማት እየሰራው 2 አመት ሞልቶኛል፡፡ ስለዚህ ብቃት አለህ ፤ ሴቶን መምራት ትችላለህ ፤ በሴቶች እግርኳስ ላይ ያለው ችግር ብዙ ስለሆነ መፍታት ትችላለህ ተብዬ ነው ኃላፊነት የተረከብኩት፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ለሴቶች እግርኳስ ትኩረት በመስጠት የሚታወቀው የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ በዛ በከፍተኛ አመራርነት ለሴቶች ትኩረት ሰጥቼ ሰርቻለሁ፡፡

‹‹ ብቃት ስለሌለው ነው የሚባለውም ነገር ከ11 ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል መካከል ለካፍ ከተላኩት በትምህርትም በብቃትም ስላመኑብኝ ይመስለኛል የመረጡኝ፡፡ ችግር ሲመጣ ብቃት የለውም መባሉ ትክክል አይደለም፡፡ ››

 

ስለተፈጠረው ስህተት..

ብሄራዊ ቡድናችን መሳተፍ አለመሳተፉን እንዲያሳውቅ ከካፍ ኦገስት 14 ደብዳቤ ተልኳል፡፡ ኦገስት 17 በድጋሚ ተመሳሳዩ ደብዳቤ ተላከ፡፡ ኦገስት 28 ራሱ ደብዳቤ ተልኳል፡፡ ቀነ ገደቡ በሚያበቃበት እለትም ኦገስት 31 ላይ ተልኳል፡፡ ከዛ ካፍ መልስ በማጣቱ ነው ከውድድሩ ውጪ የሆንነው፡፡

በሌላ በኩል እኔ ለካፍ ስብሰባ የተጠራሁት ኦክቶበር 20 ነው ካፍ እንድንወዳደር ያቀረበው ጥሪ ቀኑ ካለፈ ከ1 ወር ከ20 ቀን በኋላ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከማጣርያው የወጣው እኔ በተካፈልኩበት ስብሰባ ላይ ሳይሆን ከዛ በፊት ነው፡፡ ‹‹ሰነድ አልደረሰኝም ብሏል›› እንደተባለው አይደለም፡፡ አጀንዳው ላይ የካሜሩኑ የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ አንዱ ነበር፡፡ ድልድሉንም እናሳውቃለን ብለዋል፡፡

ስህተት የምለው ቦታ አለ፡፡ በስብሰባው ላይ የማጣርያው እጣ ድልድል እናሳውቃል እንዳሉ መናገር ነበረብኝ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት ተመዘገበ አልተመዘገበ ብዬ ጠይቄ አላውቅም፡፡ አይመዘገብም ብዬም ስላላሰብኩኝ ጥያቄውን አላነሳሁም፡፡

ከስብሰባው መልስ ሪፖርት አቅርቤ ነበር፡፡ ከ20 አመት በታች ቡድናችን ያሳየውን ብቃት መናገሬን ስናገር ከመካከላቸው አንድ ስራ አስፈፃሚ አባል ተነስቶ ነው የጨበጠኝ፡፡ ከዛ ውጪ ስላለመግባታችን የጠየቀኝ የለም፡፡ በእለቱ የካፍ ስብሰባ ላይ እጣ አልወጣም፡፡ የተመዘገቡ ሃገራት ራሱ ይፋ አልተደረጉም፡፡ ስለሄድኩ ብቻ ስላለመመዝገባችን ላውቅ አልችልም፡፡ ስለዚህ ይህ የሁሉም የኮሚቴ አባል የጋራ ተጠያቂነት ነው፡፡

 

ስለ ውሳኔው

‹‹ አቶ ጁነይዲ ከካይሮ ሲመለሱ እንደኔ የተወሰነበት አግባብ ትክክል አልነበረም፡፡ የተጠራሁት ተወያይተን ችግሩ የት እንዳለ አይተን ጥፋተኛውን ለመወሰን ነበር፡፡ አጠቃላይ ፅህፈት ቤቱ ምን አጠፋ ህዝብ ግንኙነቱ ምን አጠፋ ፣ የአይ ቲ ባለሙያዋ ምን አጠፋች የሚለውን ሳያጣሩ ነው ወደ ውሳኔው የሄዱት፡፡ እንደ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቶ ወንድምኩን የውሳኔው አካል ሊሆኑ አይገባም ብዬ ስከላከል ‹‹ራስህን ለማዳን ነው ወንድምኩንን ካልቀጣን አንተም አትቀጣም ፤ ህዝብ ከአቅም በላይ ሀኖብናል ሚድያውም ሊያስቀምጠን አልቻለም፡፡ ስለዚህ አንተ ባለቤት ስለሆንክ እገዳውን ተቀበልና ከ15 እና 2 ቀን በኋላ ይመልስሃል፡፡›› ብለውኛል፡፡

‹‹ እገዳውን አልቀበልም፡፡ ውሳኔውን ተቀበልኩ ማለት ከኔ በስተጀርባ ላሉ ወዳጆቼም ፣ ለወከለኝ ክልሌም ፣ ለልጄም ስል ባላጠፋሁት ጥፋት አጥፍቻለሁ ብዬ ማመን ጥሩ አይደለም፡፡ ጥፋታችንን አምነን በጋራ ይቅርታ እንጠይቅ ስንል መጠየቅ ካለብህ ራስህ ጠይቅ እኛ አንጠይቅም ነው ያሉት፡፡ የህዝቡንም ስሜት ለማርገብ ይህንን እገዳ ተቀበል ነው የተባልኩት፡፡ እገዳውን አልቀበልም ብዬ ወጥቻለሁ፡፡

‹‹ በሌለንበት በተወሰነ ውሳኔ ጥፋተኛ መባል የለብንም፡፡ አንድ ወንጀለኛ እኮ ወንጀለኛነቱ የሚረጋገጠው ጥፋት ማጥፋን ሲያምን ነው፡፡ አሁን ላይ ለተከሰተው አጠቃላይ ችግር የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአግባቡ አለመምራታችን ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ተጠያቂነቱ የሁሉም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባል፡፡

‹‹ ውሳኔው የተወሰነበት አግባብ ባለፉት 2 አመታት በፌዴሬሽን ውስጥ ያለውን የአሰራር ብልሹነት ለማስተካከል በማደርገው ጥረት ባለን ቅራኔ ነው፡፡ የቡድን መሪዎች ኢትዮጵያ እስካሉ ድረስ በሆቴል ሊያርፉ አይገባም በማለቴ ፣ በሃገሪቱ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ሲጨመር የተቀጣሪ ሰራተኞቻችን ደሞዝ እንዲሻሻል በመጣሬ ፣ በባሬቶ ቅጥር እና ሰውነት ስንብት ምክንያት ፣ ሊጉ ሲፈርስ አግባብ አይደለም ይቀጥል ከፍተኛ ሊጉ ላይ ቅሬታ ያላቸው አካላት ሰሚ ሊያገኙ ይገባል ስላልኩ ፣ ለአሰራር የተቃና እንዲሆኑ ስታገል ሳላስበው ግላዊ ስሜት እንዲገቡ ያደረጉ ይመስለኛል፡፡ የትላንትናው (ሀሙስ) ውሳኔ ስሜት ይህንን ያንፃበርቃል፡፡ አሁንም ቢሆን የፅህፈት ቤት ኃላፊው (ዘሪሁን ቢያድግልኝ) ራሳቸውን ከስራው አግልለዋል፡፡ ጥሩ ነው ነገር ግን ፅህፈት የሚመራው ፕሬዝዳንቱ ነው፡፡ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በተፈጠረው ችግር ፣ ስራ አስፈፃሚ አቀባበል ሲያደርግ ተገኝቶ አቀባበል ያለማድረግ ፣ ሊግ አለመምራት ፣ ችግሮችን መፍትሄ አለመስጠት እና የመሳሰሉት ተደራርበው የስራ ብቃታቸው አነስተኛ ስለሆነ ሊመሩ አይችሉም ብዬ በቀናነት ይልቀቁ ብያለሁ፡፡ እርምጃ ያልተወሰደው በጥልፍልፍና በቡድን ስራ ስለሚሰራ ነው፡፡ ጥፋት ሲጠፋ አይደለም ራሳቸውን የሚያገሉት፡፡ ››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *