የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአለም ዋንጫ ማጣርያ ከኮንጎ አቻው ጋር በሜዳው ባደረገው ጨዋታ 4-3 ተሸንፎ የማለፍ እድሉን አጣብቂኝ ውስጥ ከትቷል፡፡
ኮንጎዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ከመስመር ወደ ውስት በተዳጋጋሚ በመግባት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተረጋግቶ የመጫወት ችግር ተስተውሏል፡፡
ኮንጎዎች በ16ኛው ፣ በ23ኛው ደቂቃዎች የግብ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን በ21ኛው ደቂቃ ከ2ኛ ቅጣት ምት ቦፉውማ ወደ ግብ የመታው ኳስ ስዩም ተደርቦ ወደ ውጪ አውጥቷታል፡፡
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጀመርያውን የግብ እድል ለመፍጠር ግማሽ ሰአት ጠብቋል፡፡ በ29ኛው ደቂቃ ሽመልስ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የመታው ከኳስ በግቡ አግዳሚ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡
በ32ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ከዳዊት ፍቃዱ የተሸገረለትን ኳስ ጌታነህ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
በ40ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ የተከላካዩ ባቤሌ እና ግብ ጠባቂውን ማፉምቢ የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ኢትዮጵያን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶርያው አጥቂ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብ ሲያስቆጥር ከ1 አመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
ኮንጎዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ከ2 ደቂቃ በኋላ ከማእዘን አካባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት ቲዬቪ ቢፎውማ ወደ ግብነት ቀይሯታል፡፡ ለግቧ መቆጠር የታሪክ ጌትነት ስህተት ተጠቃሽ ነበር፡፡
የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተጠናቀቀው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ነበር፡፡ በ2ኛው አጋማሽ ባልተጠበቀ ሁኔታ 5 ግቦች ተቆጥረዋል፡፡
በ61ኛው ደቂቃ ቢፎውማ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ኦንዳማ ኮንጎን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡
በ69ኛው ደቂቃ ባፎውማ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ታሪክ ጌትነት አክሽፎበታል፡፡
በ70ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከፍጹም ቅጣት ምት ግራ ጠርዝ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡
በ73ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜደ የገባው ማላንጋ ያሻማው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ግብ እድልነት ቢቀየርም ታሪክ ወደ ውጪ አውጥቶታል፡፡
በ74ኛው ደቂቃ ከማእዘን ምት የተሻገረውን ኳስ አምበሉ ንጋንጋ በግንባሩ በመግጨት የኮንጎን መሪነት ወደ 3-1 አስፍቶታል፡፡
በ80ኛው ደቂቃ ባፎውማን ቀይሮ የገባው ቢንጉላ የነጂብ ሳኒን ስህተት ተጠቅሞ 4ኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
የኢትዮጵያ የማለፍ ተስፋ ወደ ዜሮ በተጠጋበት ሰአት ዳዊት ፍቃዱ በ81ኛው ደቂቃ ከሽመልስ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮታል፡፡
በ87ኛው ደቂቃ በጋቶች ተቀይሮ የገባው በሀይሉ ግርማ ከማእዘን የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ ሞክሮ የኮንጎ ተከላካዮች ከመስመር አውጥተዋታል፡፡
በ88ኛው ደቂቃ ማላንጋ የኮንጎን መሪነት ወደ 5 የሚያሰፋበት እድል ቢያገኝም በማይታመን ሁኔታ አምክኗታል፡፡
በ90ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ ለኢትዮጵያ 3ኛ ግብ አስቆጥሮ ጨልሞ የነበረው የማለፍ ተስፋ ላይ ጭላንጭል ተስፋ ዘርቶበታል፡፡ ጨዋታውም በኮንጎ 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የመልሱ ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ በብራዛቪል ይካሄዳል፡፡