ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ደደቢት

ከነገ ጀምሮ ከሚደረጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች መካከል ቀዳሚ በሆነው የጅማ አባ ጅፋር እና ደደቢት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በመጨረሻ 15ኛው ሳምንት ጨዋታዎቻቸው ሽንፈት የገጠማቸው ጅማ አባ ጅፋር እና ደደቢት ነገ 09፡00 ላይ በጅማ ይገናኛሉ። ወደ ሀዋሳ አቅንቶ በደቡብ ፖሊስ ያልተጠበ የ6-1 ሽንፈት ደርሶበት የተመለሰው ጅማ አባ ጅፋር አሁንም ከታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ከፍ ማለት አልቻለም።በዚህ ሳምንትም በተጨዋቾች ደሞዝ ጉዳይ የልምምድ መርሐ ግብርን እስከማቋረጥ ደርሶ የነበረው ክለቡ በሊጉ ፉክክር ውስጥ የሚኖረውን ቦታ ለመወሰን ከሚያስችሉት አራት ተስተካካይ ጨዋታዎች ውስጥ አንዱ በሆነው የነገው ጨዋታ ነገሮችን በፍጥነት ማስተካከል ይጠበቅበታል። ጅማ አሸንፎ ወደ አስረኛነት ከፍ የማለት ዕድልን መያዙ ለጨዋታው ያለውን ቦታ ከፍ የሚያደርገው ሲሆን ከሜዳ ውጪ ላሉበት ችግሮች መቀረፍም አንድ እርምጃ ሊሆንለት ይችላል። አባ ጅፋር የልምምድ ጊዜን ካላሟላው ዲዲዬ ለብሪ መሰለፍ አጠራጣሪነት እንዲሁም ከዘሪሁን ታደለ አለማገገም በቀር ከሆላንድ የተመለሰው ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄዬን ጨምሮ በሙሉ ስብስቡ ደደቢትን እንደሚያስተናግድም ይጠበቃል።

በአዲስ አሰልጣኝ ሹመት እና የውጪ ተጨዋቾች ቅጥር ሽር ጉድ ሲሉ የከረሙት ደደቢቶች በመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ነው ወደ ጅማ የሚያቀኑት። በሊጉ ግርጌ መቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን ከበላያቸው ካሉት ስሑል ሽረ እና ደቡብ ፖሊስ ጋር በሰባት ነጥብ ልዩነት አንሰው መገኘታቸው ለሰማያዊዎቹ ቀጣይ እጣ ፈንታ እጅግ አስጊ ይመስላል። ከባድ ከሆነው የነገው ተልዕኳቸው በድል ከተመለሱ ይህን የነጥብ ልዩነት በማጥበብ የሁለተኛ ዙር ተስፋቸውን በመጠኑም ቢሆን ማለምለም ቢችሉም ሽንፈት ደግሞ በተቃኒው አጣብቂኝ ውስጥ የሚከታቸው ይሆናል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ያለምንም ጉዳት እና ቅጣት ለጨዋታው ከመድረሱ ባለፈ የዓለምአንተ ካሳ ከጉዳት መመለስም በጥሩ ዜና የሚነሳለት ይሆናል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ጅማ አባ ጅፋር ወደ ሊጉ በመጣበት የአምናው የውድድር ዓመት ደደቢትን በገጠመባቸው ሁለት ጨዋታዎች የ2-1 እና የ3-0 ድሎችን አሳክቷል። ለደደቢት የመጀመሪያው ዙር የ2-1 ሽንፈት ከስድስት ተከታታይ ድሎች በኋላ የገጠመውም ነበር።

– በሜዳው የዓመቱን አምስተኛ ጨዋታ የሚያደርገው ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን ሽንፈት ያልገጠመው ቢሆንም ሦስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቶ በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው ድል የቀናው።

– ከመቐለ ውጪ ስድስት ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት 12 ግቦችን አስተናግዶ ያለምንም ነጥብ የተመለሰ ሲሆን ማስቆጠር የቻለውም አንድ ግብ ብቻ ነው።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው የሚመራ ይሆናል። አርቢትሩ እስካሁን በስድስት ጨዋታዎች አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ ሲያሳልፍ አንድ የቀይ እና 19 የቢጫ ካርዶች መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ዳንኤል አጃዬ

ዐወት ገብረሚካኤል – ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ኤልያስ ማሞ – አክሊሉ ዋለልኝ – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ዳዊት ወርቁ – ኤፍሬም ጌታቸው – ዳንኤል ጌድዮን

ኩማ ደምሴ – የዓብስራ ተስፋዬ

ዳግማዊ ዓባይ –ዓለምአንተ ካሳ – አሌክሳንደር ዐወት

አኩዋር ቻሞ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *