ሪፖርት | መከላከያ እና ድሬዳዋ ያለ ግብ ተለያይተዋል

ከ3ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የመከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂዶ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

መከላከያ በ15ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈው ቡድኑ ውስጥ የግራ መስመር ተከላካዩ ዓለምነህ ግርማን በሙሉቀን ደሳለኝ ሲተካ በተመስገን ገብረኪዳን ቦታ ደግሞ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሮ የነበረው ፍቃዱ ዓለሙን ተጠቅሟል። በድሬዳዋ በኩል በተመሳሳይ ሳምንት በመቐለ በተሸነፈው ቡድን ላይ በተደረገው ለውጥ ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ በፍሬው ጌታሁን የተቀየረ ሲሆን ከጋብቻ ሥነ ስርዓታቸው የመተለሱት ረመዳን ናስር እና ሚኪያስ ግርማም በኃይሌ እሸቱ እና ሳሙኤል ዮሀንስ ቦታ ጨዋታውን ጀምረዋል።


በሴቶች ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር የተደረገው የመከላከያ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ እስከ መለያ ፍፁም ቅጣት ምቶች በመድረሱ ምክንያት ጨዋታው በ30 ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረ ነበር። በአመዛኙም የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ሂደት በድሬዳዋ ሜዳ ላይ የቆየ ሲሆን የመከላከያዎች የእንቅስቃሴ እና የሙከራ የበላይነትም ታይቶበታል።

የተሻለውን የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በመያዝ በቀኝ የቡድኑ ወገን ሽመለስ ተገኝንም ባሳተፈ መልኩ አጥቅተው ለመጫወት የሞከሩት መከላከያዎች ኳስ በመያዛቸው መጠን በድሬ ሳጥን ውስጥ መገኘት ባይችሉም ንፁህ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠራቸው ግን አልቀረም። ከነዚህም መሀል 11ኛው ደቂቃ ላይ ከምንይሉ በተነሳ እና ዳዊት ማሞ ባደረሰው ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ ሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገው መከራ ተጠቃሽ ሲሆን በሁለት አጋጣሚዎች ምንይሉ ያመከናቸው ኳሶች ግን ወርቃማ የሚባሉ ነበሩ። ምንይሉ በ15ኛው ደቂቃ ዳዊት ማሞ ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ አንተነህ ተስፋዬ ሲደረብ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ጋር ተገናኝቶ ሲስት 33ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂውን እና ተከላካዮችን አታሎ ከቅርብ ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ደግሞ በተከላካዮች ጥረት ከመስመር ላይ ተመልሶበታል። ከዚህ ውጪ መከላከያዎች በበርካታ ቅብብሎች እስከ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ እና የሜዳውን የጎን ስፋትም በአግባቡ ለመጠቀም ሲሞክሩ ቢታዩም በዳዊት ማሞ እና ሙለቀን ደሳለኝ ያደረጓቸው የርቀት ሙከራዎችም ኢላማቸውን መጠበቅ አልቻሉም።


በተመሳሳይ ኳስ መስርተው ለመውጣት ያሰቡ የመሰሉት ድሬዎች ሐብታሙ ወልዴን ፊት ላይ በማስቀረት እና አምስቱን አማካዮቻቸውን ወደ ተከላካይ ክፍላቸው በማስጠጋት በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ፊት ለመሄድ ሞክረዋል። በዚህ ረገድ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ገናናው ረጋሳ በግል ጥረቱ ወደ ውስጥ ለመግባት የሚያደርጋቸው ጥረቶች እና በግራ በኩል በአማካይነት የተሰለፈው ራምኬል ሎክ ከሚደርሱት ኳሶች ወደ ሳጥን ውስጥ ለመግባት የሚሞክርባቸው እንቅስቃሴዎች ተጠቃሽ ነበሩ። በዚህም 41ኛው ደቂቃ ላይ ከሁለቱ ተጫዋቾች ጥምረት ራምኬል ሳጥን ውስጥ ከግራ ያሻማውን ኳስ ምንያህል ይመር በግንባር ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ቅብብሎቹን ከራሱ ማዳ ይዞ ማለፍ ሲቸገር መሀል ላይ ከመከላከያ ተጫዋቾች በሚነጠቁ ኳሶች ለመክፈት የሚሞክራቸው ጥቃቶች ፊት ላይ በቁጥር ማነስ እና በደካማ የማጥቃት ሽግግር ሲከሽፍበት ታይቷል። የተሻለ በነበረው አጋጣሚም 21ኛው ደቂቃ ላይ ገናናው ረጋሳ ሚኪያስ ግርማ በተከላካዮች መሀል በሰነጠቀለት ኳስ ያደረገው ሙከራ ወደላይ ተነስቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር የተቀዛቀዘ ነበር። የአሰልጣኝ ስምኦን አባይ በድን ከዕረፍት መልስ አማረ በቀለን በረመዳን ናስር በመለወጥ እና በመስመር ተከላካይነት በመጠቀም ገናናው ረጋሳን ረመዳን ከቀኝ በመነሳት ሲጫወትበት ወደ ነበረው የአማካይ ቦታ ቀይሯል። ለውጡ በርግጥም በገናናው በኩሉ አልፎ አልፎ ከመልሶ ማጥቃት በሚነሱ ኳሶች ብልጭ ብለው የሚጠፉ የማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያሳየንም በድኑን የበላይ ማድረግ የቻለ ግን አልነበረም። የድሬ መጠነኛ የማጥቃት ፍላጎትም ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሄዶ ወደ መከላከሉ በማድላት አንዱን ነጥብ በማስጠበቅ ላይ ትኩረት አድርጓል። 69ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል በመልሶ ማጥቃት ከተገኘ ኳስ በቀኝ መስመር ከሀብታሙ ተቀብሎ የሞከረው እና ወደላይ የተነሳበት ኳስም ብቸኛው የአጋማሹ የቡድኑ ሙከራ ነበር።


እንደመጀመሪያው ሁሉ የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ያልተነጠቀው መከላከያ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል የነበረውን ብልጫ ግን መድገም አልቻለም። ምንይሉ ወንድሙን ይበልጥ ወደ አማካዮቹ ቀርቦ እንዲጫወት በማድረግ ተጨማሪ የመቀባበያ አማራጮችን ለመፍጠር የሞከሩት መከላከያዎች ፍፁም ገብረማርያምንም በፍቃዱ ለውጠው በማስገባት ፊት ላይ ስል ለመሆን ቢሞክሩም የድሬን የተደራጀ መከላከል መስበር ሳይችሉ ቀርተዋል። የተጋጣሚያቸው መከላከል በጠነከረባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች በተረጋጋ ሁኔታ ኳስ ይዘው የድሬዳዋን ተጫዋቾች ወደ መሀል ሜዳ ስበው ክፍተት ለማግኘት የሞከሩበት እና ረጃጅም ኳሶችንም ወደ ፊት በመጣል ያደረጓቸው ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል።
86ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ከወጣበት ሙከራ ውጪም ፍሬው ጌታሁንን መፈተን ሳይችሉ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።

በውጤቱም መከላከያ በነበረበት 11ኛ ደረጃ ላይ ሲቆይ ድሬዳዋ ከተማ አንድ ደረጃ በማሻሻል ወደ 12ኝነት ከፍ ብሏል። በቀጣይ ሁለቱም በድኖች የቀራቸውን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አከናውነው የመጀመሪያ ዙር ውድድራቸውን ያጠቃልላሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *