ከፍተኛ ሊግ | ወልቂጤ መሪነቱን የማስፋት እድሉን አምክኗል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው በምድብ ለ መሪ ወልቂጤ ነጥብ ተጋርቶ መሪነቱን የማጠናከር እድል ሲያመክን በምድብ ሐ አርባምንጭ ተሸንፎ ከሀዲያ ሆሳዕና የነበረውን ልዩነት ማጥበብ ሳይችል ቀርቷል።

ወልቂጤ ላይ ወልቂጤ ከተማ ከ የካ ክፍለከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ፈጣን እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ እንግዶቹ ጥሩ አጀማመር በማድረግ በሁለት አጋጣሚዎች በዮናስ ሰለሞን እና ንጉሴ ጌታሁን አማካኝነት የወልቂጤን ግብ ፈትሸዋል። ወልቂጤዎች በአንፃሩ በ9ኛው እና 10ኛው ደቂቃ በአህመድ ሁሴን መሪ ሊያደርጋቸው የሚችል የግብ ሙከራዎች አድርገዋል።

በመስመሮች በኩል በሚሻሙ ኳሶች ግብ ለማግኘት ያለመ እንቅስቃሴ ያደረጉት ወልቂጤዎች የግብ ሙከራ ማድረጋቸውን በመቀጠል በ17 ኛው ደቂቃ ተስፋዬ በቀለ ከቀኝ መስመር የተሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶት የግቡን አግዳሚ ታካ ስትወጣበት በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ብስራት ገበየው በ28ኛው ደቂቃ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ የየካው ግብጠባቂው አድኖበታል። በ34ኛው ደቂቃ ተመስገን ደረሰ በግንባሩ ገጭቶት በግቡ ቀኝ አግዳሚ ታካ የወጣችበት አጋጣሚም ወልቂጤን ቀዳሚ ማድረግ የምትችል እድል ነበረች። የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ሐብታሙ አክርሮ የመታውን ኳስ የግቡን የግራ አግዳሚ ታካ የወጣችበት አጋጣሚም ሌሌዋ ተጠቃሽ የወልቂጤ ሙከራ ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ እንግዳው ቡድን በእንቅስቃሴ ከመጀመሪያው አጋምሽ ተሽሎ ሲቀርብ የምድቡ መሪ ወልቂጤ ከተማም ግብ አስቆጥሮ መሪነቱን ማጠናከርን ያለመ እንቅስቃሴ አሳይቷል። በዚህም 52ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ተስፈኛው ተጫዋች አብዱልከሪም ወርቁ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት ብስራት ሲያሻማው ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አሳልፈው መኮንን ወደ ግብነት ለውጦ ባለሜዳዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ኳሱን ይዘው ለመጫወት የሞከሩት የካዋች ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ሲደርሱ ታይተዋል። በ59ኛው ደቂቃ ተመስገን ደረሰ አክርሮ የመታውን ኳስ ተደርበው የመለሱት የካዎች ኳሱን ወደ መልሶ ማጥቃት በመቀየር የፈጠሩትን የግብ እድል በአግባቡ መጠቀም ችለዋል። ዮናስ ሰለሞን ሳስቶ የነበረው የወልቂጤ ተከላካይ ክፍል በማለፍ ያሻገረትን ኳስም ንጉሴ ጌታሁን ወደ ግብነት ለውጦት አቻ መሆን ችለዋል።

ወደ መሪነት ለመመለስ ተጭነው መጫወት የፈለጉት ወልቂጤዎች ስኬታማ ባይሁኑም በርካታ የአየር ኳሶችን መሞከር ችለዋል። በተለይም 67ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ታደሰ የየካውን ግብ ጠባቂ መውጣት ተመልክቱ በጭንቅላቱ ላይ ከፍ አድርጎ የሰደዳት ኳስ የግቡን አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች። በ78ኛው ደቂቃ ሐብታሙን ተክቶ የገባው ኤደም ኮድዞ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ንጉሴ ጌታሁን በቀኝ እጁ ቢነካውም የእለቱ ዳኛ በዝምታ ማለፋቸውን ተከትሎ ዳኛው ላይ ተቃውሞ የተሰማ ሲሆን የየካ ግብ ጠባቂ ከዳኛው ጋር አላስፈላጊ ንግግር ሲያደርግ ታይቷል። ወልቂጤዎች በቀሩት ደቂቃዎችም ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ቢጫወቱም ተጨማሪ ጎል ሳይጠናቀቅ 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ደጋፊዎች ዳኛው ላይ ተቃውሞ ከመቼውም በተለየ መልኩ ቆመው ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን ጥቂት ወደ ሜዳ የገቡ ደጋፊዎች ጥቃት ለማድረስ እንዳይሞክሩ የክልሉ ጥበቃ ኃይል እንዲሁም የደጋፊዎች ማኅበር፣ የወልቂጤ አመራሮች እና የክለቡ አሰልጣኝ ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ነበር።

በምድብ ሐ በተደረጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ በሜዳው ከፋ ቡናን 1-0 ማሸንፍ ችሏል። ሺንሺቾ ላይ ደግሞ ከመመራት ተነስቶ አርባምንጭ ከተማን 2-1 አሸንፏል። ቢሾፍቱ ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከጅማ አባቡና እንዲሁም ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከነቀምት ያለምንም ጎል የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *