የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ትናንት አካሄደ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የክለቡ የቦርድ አመራሮች እና ደጋፊዎች በተገኙበት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል። 

ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ፣ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝደንት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም እንዲሁም አዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሃ በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን የስፖርት ማህበሩ የቦርድ አመራሮች እና በርካታ ደጋፊዎች የታደሙበት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ አከናውኗል።

የጉባዔውን መክፈቻ ንግግር እና በ2010 ስፖርት ማኅበሩ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትን የቦርድ ሰብሳቢው አቶ አብነት ገብረመስቀል ያቀረቡ ሲሆን ተካታዮቹ ነጥቦች በንግግራቸው ውስጥ ተካተዋል።

* ከአጋር ድርጅቶች ጋር የስፖንሰርሺፕ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ከአስር እስከ ከአስራ አምስት ዓመት የሚያቆይ የስፖንሰርሺፕ ውል ከደርባን ፣ ከሞሐ ፣ ከቢጂአይ ፣ ከዳሽን ባንክ ፣ ከሆራዘን አዲስ ጎማ… … ወዘተ ተፈፅሟል።

* በገና በዓል ባዛር ውጤቱ አመርቂ ባይሆንም ከ5.2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ተችሏል።

* የሼር ኩባንያ ለማቋቋም fair fax consulting ከተባለ አማካሪ ድርጅት ጋር በመነጋገር ጥናቱ ተጠናቆ ለጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ ቀርቧል።

* የአባላትን የአመዘጋገብ ስርዓትን ለማዘመን ክፍያ ፋይናንሽያል ቴክኖሎጂ ከሚባል ኩባንያ ጋር ውል ተፈፅሞ በአሁኑ ሰዓት ለውሳኔ ቀርቦ ስራውም ተጀምሯል።

* የደጋፊውን ፍላጎት ለማርካት ባይችልም በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት የተመረቱ ከ13 ሺህ በላይ ማሊያዎች ሽያጭ ተከናውኗል።

* ክለቡ ከአያት መንደር ከ63 ሺ ካሬ ሜትር ላይ ስታድየም ለማስገንባት ጅምሮ ግንባታው 20% ከደረሰ በኋላ ተቋርጧል። ችግሩ የፋይናስ አቅም ማነስ በመሆኑ የተቋረጠውን ስራ ለማስጀመር ዝግጅት የተደረገ ነው።

* ክለቡ ከተለያዩ ምንጮች 49,717,438,45 ብር ገቢ ሲሰበስብ አጠቃላይ ወጪው ደግሞ 44,251,602,67 ሆኖ ሲመዘገብ ከወጪ ቀሪ 5,465,835,78 ብር አስመዝግቧል። በተያያዘ ለመንግስት የታክስ ግብር ብር 7,554,494,70 ገቢ ተደርጓል።

* ቦሌ የሚገኘው የልምምድ ሜዳ ለልማት በመፈለጉ ምክንያት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስታድየም መገንቢያው አጠገብ 10,000 ሜትር ካሬ ምትክ ቦታ ተገኝቷል።

* የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ ዓመታዊ ውድድር በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል።

* አባላቶች እና ደጋፊዎች በየዓመቱ በሚሳተፉባቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች ደም በመለገስ ፣ የመማርያ ቁሳቁሶችን በማበርከት ፣ የህክምና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የተለያዩ ግለሰቦች ድጋፍ በማድረግ እና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን የተሳካ ስራ ተተሰርቷል።

በመቀጠል የበጀት ዓመቱን የሂሳብ ምርመራ ሪፖርት በአቶ ዘመድሁን አዳነ የቀረበ ሲሆን ከተለያዩ ገቢዎች ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተገኘ እና ለተለያዩ የስራ ወጪዎች 44 ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣ። ከወጪ ቀሪ 4 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳለ እንዲሁም የማኅበሩ አጠቃላይ ሀብት ወደ 97 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የሚያብራሩ ዝርዝር የኦዲት ሪፖርቶችን አቅርበዋል። በቀረበው የኦዲት ሪፖርት ዙርያም ከጉባዔው አባላት ሙያዊ የሆኑ ጥያቄዎች ቀርበው በአቶ ዘመድሁን ምላሽ ተሰቶባቸው ጉባኤው የቀረበውን የበጀት ዓመቱን የሂሳብ ምርመራን በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

በቀጣይም አቶ አብነት ገብረመስቀል የ2010 የስራ ዘመን ያቀረቡትን ሪፖርት መሰረት በማድረግ ከጉባዔው አባላት ዘንድ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል። ከነዚህም ውስጥ

* ክለቡ የደጋፊ ማህበር ሊያቋቁም ይገባል።

* የማልያ አቅርቦት የደጋፊውን ፍላጎት ያገናዘበ አይደለም በጣም ከፍተኛ እጥረት አለ።

*የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር ሂደት እና የሚመጡበት መንገድ እንዴት ነው ?

* የስፖንሰር ገቢ አነስተኛ ነው ከዚህ በላይ ሌሎች ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶችን ፣ እና ባለኃብቶችን ለማሳተፍ ለምን አልተፈለገም ?

* ብዙ ነገሮች ይሰማሉ፤ እናያለን። የተጫዋቾች ዲሲፒሊን ችግር ይታሰብበት።

* የቴሌቭዥን ስርጭቱ ይጀመራል ቢባልም እስካሁን አለመጀመሩ ምክንያቱ ምንድን ነው ?

* የአክስዮን ሽያጩ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ? የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በመቀጠል ለቀረቡት ጥያቄዎች አቶ አብነት ገብረ መስቀል እና አቶ ንዋይ በስፋት ምላሽ ሰጥተውባቸዋል። የደጋፊ ማኅበር መቋቋምን በተመለከተ አቶ ነዋይ በሰጡት ምላሽ በማኅበር ላይ ማኅበር ማቋቋም እንደማይቻል፤ አስቀድሞ ክለቡ ሲቋቋም ደጋፊዎች ያሉበት የስፖርት ማኅበር መሆኑን እና ለማቋቋም ከተፈለገ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ክለቡን ማፍረስ እንደሚያስፈልግ ገለፀዋል። ክለቡ በራሱ የሚመራው በደጋፊ ማኅበሩ እንደሆነም ገልፀዋል። ሆኖም በየአካባቢያቹ በፈለጋችሁት መንገድ ተደራጅታቹ ክለቡን በማገዝም ሆነ ማህበራዊ ድጋፍ በማድረግ ማህበራትን ማቋቋም ትችላላችሁም ብለዋል።

ማልያን በተመለከተ አቶ ንዋይ ሲመልሱ ” በሚፈለገው ደረጃ ማልያ ባለማድረሳችን ይቅርታ እንጠይቃለን። እስካሁን ከ13 ሺህ በላይ ማልያ እንደቀረበ እና በቀጣይ ከዚህ በተሻለ የደጋፊውን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ማልያዎች ይቀርባሉ” ብለዋል።

የውጪ ተጫዋቾች ምልመላን እና ሌሎች ስፖንሰር ፍለጋን አስመልክቶ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በሰጡት ምላሽ ደግሞ ” ብቁ ባለሙያዎችን በመደብ ያሉበት ሀገር ድረስ በመላክ ምልመላ እናደርጋለን። አሰልጣኞቹ ይጠቅማል ሲሉ እናስፈርማለን። እንደተጠበቁ ሳይሆኑ ሲቀር እናሰናብታለን። በእግርኳስ የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው የሚከሰቱት። አሁንም በአሰልጣኙ ምርጫ የውጪ ተጫዋቾች አስመጥተናል ሁለተኛው ዙር ላይ የምንጠቀም ይሆናል። ሌሎች ስፖንሰር አድራጊዎች ከእኛ ጋር ለመስራት ከፈለጉ በራችን ክፍት ነው ስፖንሰር ማድረግ ይችላሉ። ሆኖም እንደ ቢጂ አይ ያሉ ባለውለታዎቻችንን መርሳት የለብንም እስካሁንም በስፖንሰር ሺፕ በየዓመቱ 35 ሚሊየን ብር ማግኘት ቀላል አይደለም እንደ ትንሽ መወሰድ የለበትም። አሁን ከደርባን እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በከፍተኛ ሁኔታ አዲስ ውል ተዋውለናል። ይህ ከስፖንሰር የምናገኘውን ገቢ ክለቡን ያስድጋል።” ሲሉ ቀጥለውም ” ተጫዋቾችን መምራት አስቸጋሪ ነው። በአሁን ሰዓት አሰልጣኝ ሳይሆን ፖሊስ ነው የቀጠርነው። የዲሲፒሊን ችግር እንዳለ እንሰማለን ፤ ችግሩን ለመቅረፍም እንሰራለን። እናንተም የምታዩት ነገር ካለ ጥቆማ ስጡን እርምጃ እንወስዳለን። የቴሌቭዥን ስርጭትን በተመለከተ እየሰራንበት ነው። ቀስ በቀስ ጥናቱን አጥንተን ስንጨርስ ወደሚቀጥለው ስራ እንገባለን። መጀመራችን የማይቀር መሆኑን ላረጋግጥላቹ እወዳለው” ብለዋል።

የቀረበውን ዓመታዊ ሪፖርትን ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ካፀደቀ በኋላ የቀጠለው ጠቅላላ ጉባዔው የ2011 የስራ ዘመን ዝርዝር ዕቅዶችን በአቶ ንዋይ አማካኝነት አቅርቧል። በዚህም የክለቡን የፋይናንስ ምንጮች ማስፋት እና ማጠናከር፣ የማርኬቲንግ፣ ፕሮሞሽን እና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ማጠናከር፣ በውድድሮች የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እና ሌሎች ዝርዝር ዕቅዶች ቀርበዋል።

ከቀረቡት ዕቅዶች መካከል የደንብ ማሻሻያ ይፈልጋሉ በተባሉ ጉዳዮች ለምሳሌ የአባላት ምዝገባ እና መዋጮ አሰባሰብ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን መዋጮን በተመለከተ ከ10 ብር ጀምሮ እንዲሆን ፣ አንድ ግለሰብ አባል ሆኖ ለመመዝገብ በመጀመርያ የስራ አመራሩ ቦርድ በሚያወጣው የአፈፃፀም ደንብ መሰረት ሚጠየቀውን ግላዊ መረጃ ማቅረብ እንዳለበት አባል ሆኖ ለመመዝገብ ያቀረበው ጥያቄ በስራ አመራሩ ቦርድ ወይም ከስራ አመራሩ ቦርድ በሚወከለው አካል ተጠንቶ ተቀባይነት ካገኘ ብቻ ተቀባይነት እንደሚኖረው የሚሉ ሀሳቦች ተካተውበት ፀድቋል።

በማስከተል በአክሲዮን ሽያጩ ዙርያ በባለሙያዎች ሲጠና የቆየው ጥናት ይፋ ሆኗል። አክሲዮኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሼር ካምፓኒ የሚል ጊዜያዊ ስያሜ ሲኖረው ወደ ፊት የ244 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚኖረው ተነግሯል። የአክስዮን ሽያጭ መነሻ ዋጋ 1000 ብር እንደሚሆን ፣ ከመጋቢት 23 ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሽያጭ እንደሚከናወን ፣ ዝርዝር መረጃዎችን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን እንደሚነገር በመግለፅ ባለሙያዎቹ ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል። ጉባኤውም በደስታ ከመቀመጫው በመነሳት የአክስዮን ሽያጩ እዚህ በመድረሱ አመስግኗል።

ቦሌ የሚገኘው የክለቡ የልምምድ ሜዳ በልማት ምትክ በመወሰዱ የተሰጠው 10ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የቀድሞ የክለቡ የቦርድ አባል የነበሩት ባላሀብቱ አቶ ጀማል የልምምድ ሜዳውን ፣ የተጫዋቾች ማረፊያ ፣ የመታጠብያ ሻወር እንዲሁም ሌሎች የሚያስፈልጉትን ወጪዎች በሙሉ እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል። ደርባን ሲሚንቶም የሲሚንቶ አቅርቦቱን እንደሚሸፍን በስራ ኃላፊው አማካኝነት አስታውቋል።

በመጨረሻም የዕለቱ የክብር እንግዳ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዘደንት የመዝግያ ንግግር አድርገው ጉባኤው በስኬት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *