በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ አዘጋጅነት የሚደረገው የ2016ቱ የአፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና (ቻን) የምድብ ድልድል ዛሬ የ16ቱ ተሳታፊ ቡድኖች ተወካዮች በተገኙበት በኪጋሊው ሴሬና ሆቴል ይፈፀማል።
የውድድሩ ተካፋይ ቡድኖች ከዚህ በፊት በነበሩ የቻን ውድድሮች ላይ ባስመዘገቧቸው ውጤት መሰረት በ4 ቋቶች ተመድበዋል። (በአንድ ቋት ያሉ ቡድኖች እርስ በእርስ አይገናኙም) በካፍ ነጥብ አሠጣጥ መሰረትም የውድድሩ ቻምፒዮን የነበሩ 7 ነጥብ ፣ ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁ 5 ነጥብ ፣ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች 3 ነጥብ ፣ ሩብ ፍፃሜ ላይ የተጫወቱ 2 ነጥብ እንዲሁም ከምድባቸው ማለፍ የተሳናቸው 1 ነጥብ እንዲያገኙ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የ2014ቱ የደቡብ አፍሪካ ቻን ዋንጫ ላይ በ3ቱም የምድብ ጨዋታዎች በመሸነፍ በጊዜ ከውድድሩ በመሰናበቱ 1 ነጥብ ብቻ ለማግኘት ችሏል።
የተሳታፊ ቡድኖቹ ክፍፍል ይህንን ይመስላል።
ቋት 1፡ ሩዋንዳ (አዘጋጅ) ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ ቱኒዚያ ፣ ዚምባቡዌ
ቋት 2፡ አንጎላ ፣ ናይጄሪያ ፣ ጋቦን ፣ ማሊ
ቋት 3፡ ሞሮኮ ፣ ኡጋንዳ ፣ ካሜሮን ፣ ኒጀር
ቋት 4፡ ኢትዮጵያ ፣ ኮትዲቯር ፣ ዛምቢያ ፣ ጊኒ
ሩዋንዳ ውድድሩን በ3 ከተሞች በሚገኙ 4 ስታዲየሞች እንደምታስተናግድ ይፋ ያደረገች ሲሆን አዘጋጇ ሃገር የምትገኝበት የምድብ 1 ጨዋታዎች በኪጋሊው አማሆሮ ስታዲየም ይደረጋሉ። የምድብ 2 ቡድኖች በደቡባዊቷ ቡታሬ ከተማ ሲጫወቱ በኪጋሊ የሚገኘው ንያሚራምቦ ስታዲየም የምድብ 3 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። የምድብ 4 ቡድኖች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ጊሴንዪ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል።
በሃገራቸው ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ ተሳታፊ የሚሆኑበት የቻን ዋንጫ ዘንድሮ ለ4ተኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን ሩዋንዳም ውድድሩን ከጥር 7 እስከ ጥር 29 ታስተናግዳለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማጣሪያው በድምር ውጤት ኬንያን 2-0 እንዲሁም ብሩንዲን 3-2 በማሸነፍ ውድድሩን መቀላቀሉ ይታወሳል።