‹‹ ከኮንጎ የእግርኳስ ደረጃ አንፃር 4-3 ለኛ መጥፎ ውጤት አይደለም ›› አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድናቸው በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በኮንጎ አቻው በሜዳው4-3 ከተሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። የመግለጫውን ዋና ሃሳብ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

 

ስለ ሽንፈታቸው

“ለሽንፈታችን ዋናው ምክኒያት እነርሱ ከእኛ የተሻሉ መሆናቸው ነው፤ ይህ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም። እንደውም በኔ ግምት አጥቅተን መጫወት ስለነበረብን ገፍተናቸው ነው የተጫወትነው። ወደነርሱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ እንዳንገባ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል።

በጨዋታ ደረጃ ስንመለከተው መሃል ላይ በልምድም በኳስ አደረጃጀቱም በልጠውናል። የእነሱ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች ከኛዎቹ የተሸሉ ነበሩ። ነገርግን የኢትዮጵያ እና ኮንጎን የእግርኳስ ደረጃ ከማወዳደር አንፃር ከተመለከትነው 4-3 ለኛ መጥፎ ውጤት አይደለም።”

“በሲስተም ደረጃ እነርሱ ከኛ የተሻሉ ነበሩ። የእኛን አጨዋወት ተግባራዊ ማድረግ እንዳንችል አድርገውን ነበር። በብዛት በአውርፓ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያቀፈ ቡድን ስለሆነ እኛን ከጨዋታ ውጪ ማድረግ አልከበዳቸውም። እኛም ያገኘናቸውን የግብ አጋጣሚዎች አልተጠቀምንም።”

 

ስለ ጋቶች ፓኖም አቋም

“ጋቶች በተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ተበልጦ ነበር፤ በዚህም ምክንያት የመሃል ክፍላችን ላይ ክፍተት ነበረብን። ስለዚህም በሁለተኛው ግማሽ ልንቀይረው ተገደናል።”

 

ስለ ነጂብ ሳኒ

“በነጂብ ቦታ ይዘናቸው የነበሩት ተጫዋቾች ዘካሪያስ ቱጂ እና ተካልኝ ደጀኔ ነበሩ። ተካልኝ በመታመሙ፣ ዘካሪያስ ደግሞ ካለው የአካል ግዝፈት አንፃር ከኮንጎ ተጫዋቾች ጋር እኩል ዘሎ ኳስ የመግጨት ችሎታው ላይ ጥያቄ ስለነበረብን ነጁብን መጠቀም ግዴታ ሆኖብናል። ነጂብ ኳሱን በምንይዝበት ጊዜ በምንፈልገው መልኩ መጫወት ባይችልም በመከላከሉ ረገድ ግን ጥሩ ነበር።”

 

ጌታነህ ከበደ

“በፕሮፌሽናል እግርኳስ ውስጥ አንድ ተጫዋች ግብ ሊያስቆጥር ይቸላል፤ ግብ ሳያስቆጥር ለወራት የሚቆይበትም ሁኔታ ሊፈጠር ይቻላል። የዛሬው ጨዋታ ጌታነህ ተመልሶ ወደ ብቃቱ የመጣበት ጨዋታ ነው። ግብ በማስቆጠሩ ብሔራዊ ቡድኑም ተጠቃሚ ሆኗል ለራሱ ለጌታነህም ጠቅሞታል።”

የመልሱ ጨዋታ

“ኮንጎ ላይ ያለን ዕድል ማሸነፍ ብቻ ነው፤ ለማሸነፍም መቶ በመቶ ተዘጋጅተን መሄድ አለብን።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *