የፌዴሬሽኑ መግለጫ በአዲሱ የህንፃ ግዢ ዙርያ

ትላንት በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በአራት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። ከነዚህም መካከል በቅርቡ የተከናወነው የፌዴሬሽኑ ህንፃ ግዢን በዚህኛው ዘገባ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ኢሳይያስ ጂራ

የህንፃውን ግዢ በተመለከተ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ይህ ጥንስስ የተጀመረው በ2015/16 ላይ ነው። ፊፋ ከእኛ በፊት ለነበረው አመራር የ3 ሚሊዮን ዶላር በጀት ፈቀዶ ነበር። ነገር ግን በተለያየ ችግር ምክንያት (የአፈፃፀም) የተፈቀደው ገንዘብ ሳይለቀቅ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት የጊዜ ሰሌዳው በመድረሱ ገንዘቡ ሊቃጠል የነበረ በመሆኑ ጨረታ ለማውጣት ጥያቄ ላክልንላቸው። በዚህም መሠረት በሪፖርተር እና አዲዝ ዘመን ጋዜጣ ላይ በይፋ ጨረታ አወጣን። ከዚህ በኋላ የተለያዩ ችግሮች እና ፈተናዎች ነበሩ። በዚህ ጉዳይ የኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ዐወል አብዱራሂም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን ሂደት ይገልፃሉ።

ዐወል አብዱራሂም (የግዢ ኮሚቴ ሰብሳቢ)

አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወደ ስራ ከገባ በኋላ አንዱ ማሳካት አለበት ብለን ያሰብነው እና መስራት የጀመርነው የህንፃው ጉዳይ ላይ ነበር። ኮሚቴውን ከስራ አስፈፃሚ አባላት እንዲሁም ከስፖርት ኮሚሽን እና ከመሬት ልማት መሐንዲሶች በማዋቀር ሰባት ሰዎችን ወደ ስራ አስገብተናል። የመጀመሪያ ስብሰባችን ሰኔ 25 ቀን 2010 ነበር። በዚያ ወቅት ያደረግነው ከኛ በፊት የነበረውን የስራ ሂደት ግምገማ በማድረግ በጊዜው የወጣውን ጨረታ ተመልክተናል። ከዚህ ቀጥሎ ያደረግነው ጨረታው ሁሉንም መስፈርት ያሟላል ወይስ አያሟላም የሚለውን መመልከት ነበር። ያሟላ ስለነበር አንድ ነገር ብቻ (የጨረታ ሰነድ) ጨመርንበት። ይህም ህጋዊነቱን የበለጠ ያጠነክርልናል። በዚህ መንገድ የመጀመሪያው ስብስባችንን አጠናቀናል።

ሐምሌ 1 ቀን 2010 የመጀመሪያው ጨረታ በጋዜጣ ወጥቷል። ከዚህ ጨረታ በኋላ አራት ተጫራቾች የተሳተፉ ሲሆን ሁሉም አካላት (ፕሬዝዳንቱ፣ ስራ አስፈፃሚው እንዲሁም የተጫራቾች ወኪሎች) በተገኙበት ተከፍቷል። ከዚህ በኋላ በአካል ቦታው ላይ በመሄድ አራቱም ህንፃዎች ላይ ጉብኝት አድርገናል። መስፈርታችንን የሚያሟሉ ቢሆንም ህንፃው እና የሚጠየቀው ገንዘብ ተመጣጣኝ መሆን አለበት፤ ስለዚህ ምን እናድርግ ብለን መክረን ጨረታውም ሙሉ ለሙሉ ተሰርዟል።

ነሀሴ 13 ቀን 2010 በድጋሚ ሌላ ጨረታ በሪፖርተር እና አዲስ ዘመን ላይ አወጣን። በዚህኛው ጨረታ የመጡት ሁለት ተጫራቾች ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ በቂ ባለመሆኑ በድጋሚ ውድቅ ሆኖ ለሶስተኛ ጊዜ ነሐሴ 27 ቀን 2010 ጨረታ አውጥተናል። በዚህም ጊዜ ሰባት ተጫራቾች በመቅረባቸው ጥሩ አማራጮች ቀርቦልን ነበር። በተለይም አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡት ተጫራቾች ጥሩ አማራጭ አድርገን ወሰድናቸው፤ በአካልም ጉብኝት በማድረግ ቴክኒካዊ ፍተሻ አከናውነናል። ከዚህም በኋላ የመጀመሪያው ምርጫችን በ86 ሚሊዮን ብር አሸንፏል። ነገር ግን ለአሸናፊው ይፋ ሳናሳውቀው በቀጥታ ቢሮ ድረስ አስጠርተን በህንፃውም ላይ የዋጋ ቅናሽ እንዲያደርግ ሙሉ ኮሚቴው ባለበት ጠይቅነው እንደሚያስብበት ከገለፀልን በኋላ ሰኞ ጠዋት በደብዳቤ የ3 ሚሊዮን ብር ቅናሽ ማድረጉን አሳወቀን። ይህ ይዘን ከ86 ሚሊዮን ወደ 83 ሚሊዮን ብር ከቫት በፊት ማስቀንስ ቻልን። ይህ ሁሉ የሆነው ይህ ሀብት የኢትዮጽያ ህዝብ ሀብት ስለሆነ ነው።

ከጨረታው በኋላ የግዢውን ሂደት ማፅደቅ ነበረብን። የጨረታውን ቃለ ጉባዔ ወደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ መላክ ስለነበረብን ልከናል። እዚያ ከፀደቀ በኋላ የቀረን ነገር ቢኖር የክፍያ እና የርክክብ ስነስርዓት በመሆኑ የግዢ ኮሚቴው ኃላፊነቱን እና ተግባር ስራውን አጠናቋል። የጨረታው ኮሚቴ የስራ ሂደት ይህን ይመስላል።

ኢሳይያስ ጂራ

ጨረታውን አሸንፈናል ከተባባልን በኋላ የነበረው ችግር ራሱን የቻለ ራስ ምታት ፈጥሮብናል። ከፊፋ ጋር ያለውን ነገር ለመጨረስ እንቅስቃሴ ስንጀምር የ2018 በጀት ዓመት በመዘጋቱ ክፍያው የሚፈፀመው ከ2019-23 ባለው ጊዜ ነው የሚል ነገር መጣ። እኛ ደሞ እስከ 2018 ያለውን በጀት ለመጠቀም እንቅስቃሴ በመጀመራችን ይህን ለማሳካት ረጅም ጊዜያት ወስደውበናል። ከዚህ በተጨማሪ ፊፋ እያንዳንዱ ሂደታችንን ማጣራት ስለነበረበት የወሰደው ጊዜ ነበር። ህንፃው ከተገዛ በኋላ ማድረግ ስላሰብነው የስራ እቅድ ሀተታ (ቢዝነስ ፕላን) ተጠይቀን ይህንንም ማቅረብ ችለናል። ነገር ግን ይህ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ የጨረታው አሸናፊ ጨረታውን ውድቅ ማድረግ ይችል ስለነበር ከሱ ጋር ታግሶ እንዲጠብቀን መክረናል።

በ2018 ያልቅ የነበረው በጀት እንዲለቀቅልን ብዙ ጥረናል። የማታ ማታ ገንዘቡ ተለቋል። ነገር ግን በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ብዙ ፈተና እንዲሁም ግለሰባዊ የሚመስል አስተያየቶችን አሳልፈናል። ቅድሚያ የምንሰጠው ለስራ ነው። ግን ሁሌም ትችት አለ። ጋዜጣዊ መግለጫው የቆየው የ100 ብር እቃ ሰው ገዝቶ 5 ብር ቀብድ ከፍሎ እቃውን ገዛሁኝ ማለት ስለማይችችል ነው። በእኛም በኩል ስጋት ነበረብን፤ ቅድም ያልኳችሁ ችግሮች ከፊት ለፊታችን ስለነበሩ ነበር። የሆነ ሆኖ ፊፋ 500,000 ዶላር ከላከ በኋላ የመጀመሪያው ዙር የህንፃ ክፍያ ተፈፅሟል። ሁለተኛ ክፍያ ይልክ ዘንድ የመጀመሪያውን ክፍያ ህጋዊ ደረሰኞች መላክ ስለነበረብን ያንንም አድርገን ሁለተኛ ክፍያም አሁን ተልኳል።

በዚ ህንፃ ግዢ እኔ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እጅግ በጣም ደስተኛ ነን። ህንፃውን ከሚያዝያ 30 በኋላ እንረከባለን። ህንፃው የሚገኘው ወደ ወሎ ሰፈር በሚወስደው መንገድ አይቤክስ ሆቴል ፊት ለፊት ላይ ሲሆን ባለ 8 ፎቅ ነው። ይህ ህንፃ የተቋሙን ገፅታ መገንባት ይችላል ብዬ አምናለሁ። የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ሲመጣ ከዋና ጸኃፊዋ ፋጡማ ጋር ወስደን አሳይተናዋል። እርሱም በግዢው ደስተኛ ነበር። ባለፈው ቱርክ ላይ በነበረው የፊፋ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ተነስቷል። ይህ ትልቅ ነገር ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *