ፖለቲካውን እና እግርኳሱን ወደመለየት ደርሰናል – ኢሳይያስ ጂራ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በትላንትናው ዕለት ሰፊ ሰዓት የወሰደ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። በትጥቅ አቅርቦት ስምምነት፣ በህንፃ ግዢ እና በብሔራዊ ቡድን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጊዜ የወሰደው መግለጫ የተጀመረው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳነት ኢሳይያስ ጂራ የአንደኛውን ዙር ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ መቃረብ አስመልክቶ ባስተለለፉት መልዕክት ነበር። አቶ ኢሳይያስ ሊጉ በሠላማዊ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው ለዚህ አስተዋፅኦ ያደረጉትን አመስግነዋል።

” የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር ማጠናቀቂያ ላይ እንገኛለን። አጠቃላይ ጉዞውን በተመለከተ በግማሸ ዓመት ስብሰባው ላይ በሰፊ የሚታይ ይሆናል። አሁን በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መመስገን ያላባቸውን አካላት ማመሰገን ስላለብን ለማንሳት ያህል ነው። እንደምታውቁት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ለአንድ አመት ከስድስት ወር ያህል ሜዳ ላይ የነበረው ችግር የሚታወቅ ነው። ወደዚህ ስንመጣ የገጠመን አንደኛው ፈተና ይህ ነበር። ከፖለቲካው ስራ ጋር እግር ኳሱ ተቀልቅሎብን ቆይቷል። 2010 ላይ አምስት ጨዋታ ሲቀር ነበር ወደዚህ ቦታ የመጣነው። የነበረውን ፈተና እኛም እናንተም የምታውቁት ነው። ከዛ በኋላ ያሉትን ስድስት እና ሰባት ወራት ሠላማዊ እግር ኳስ እንዲፈጠር ስራ ሰርተናል። በዚህ ጉዳይ ከፖለቲካ አመራሮች፣ ከክልል እግርኳስ ፌዴሬኖች፣ ከክለቦች እንዲሁም ከሚመለካታቸው አካላት ጋር በመሆን ውይይት ተደርጓል። ከባህል እና ቱሪዝም እንዲሁም ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በመሆን የሁለቱንም ክልል (ዐማራ እና ትግራይ) አስተዳደሮች በማግኘት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ላይ መነጋገር ችለናል። የሠላም ጉዳይ የሁለቱም ጉዳይ ነው፤ የመንግስትም ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ የሁለቱም ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮች ለሠላም መስፈን የሰጡት ቦታ በጣም ትልቅ እና ምስጋና የሚገባው ነው።

” እነዚህ አካላት ለሠላም ፍላጎት እንዳላቸው፤ እኛም ፊታችንን ወደ እግርኳሱ ልማት ስራ እንዳናዞር ወጥሮ የያዘን ይህ ስለነበር ነው ለመጠቆም የፈለግኩት። ከዚህ በኋላ ግን ፊታችንን ባቀድነው መሰረት ወደ ልማት ማዞር አለብን። ብዙ ጊዜያችንን በስራ አውለን የነበረው ሠላም ለመፍጠር ስልነበር ይህ ግብ መቷል ብለን መቀመጥ ሳይሆን መንከባከብ ነው የሚያስፈልገን። አሁን ላይ ሆነን ፖለቲካውን እና እግር ኳሱን ወደመለየት ደርሰናል። ስለዚህ እግርኳሳዊ ውሳኔ መወሰን፣ የሚያጠፋው ቡድን ላይ የዲስፕሊን መመሪያው በሚፈቅደው እርምጃ መውሰድ እየጀመርን ነው። በአጠቃላይ ሁሉም ነገር የእግርኳስ ትራክ ውስጥ ገብቶ ነው ያለው። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *