ከፍተኛ ሊግ ሀ | ሰበታ ከተማ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ከተከታዮቻቸው ጋር ያላቸውን ልዩነት አስፍተዋል


የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ሲጠናቀቁ ሰበታ ከተማ እና ለገጣፎ ድል አስመዝግበው ከተከታዮቻቸው ያላቸውን ልዩነት ወደ አምስት ከፍ አድርገዋል። ወልዲያ እና ኤሌክትሪክ ደግሞ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ለገጣፎ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ አቃቂ ቃሊቲን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ቀዝቀዝ ብሎ በተጀመረው ጨዋታ በ13ኛው ደቂቃ አንዋር አብዱል ከርቀት አክርሮ በግቡ አናት ላይ የወጣችበት የግብ አጋጣሚ በለገጣፎ በኩል የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ነበር። ወደፊት ጫን ብለው የቻሉት ባለሜዳዎቹ በ18ኛው ደቂቃ ሽመክት ግርማ ያሻገረውን ኳስ ዳዊት ቀለመወርቅ የመጀመሪያዋን ጎል በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ባለሜዳውን መሪ ማድረግ ችሏል።

አቃቂ ቃሊቲዎች የአቻ ጎል ለማግኘት ሁለት ሙከራዎች አድርገዋል። ብሩክ ዳንኤል ከቆመ ኳስ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲተፋው በቅርብ ርቀት የነበሩት የለገጣፎ ተከላካዮች ያራቁበት እንዲሁም በ24ኛው ደቂቃ ጉልላት ከሁለት ተከላካዮች አምልጦ በመውጣት አክርሮ የመታውን ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ። ሆኖም በዚህ ሁኔታ ጨዋታው ቀጥሎ እያለ 32ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ቀለመወርቅ ያሻገረለትን ኳስ ፈጣኑ አጥቂ ሐብታሙ ፍቃደ ይዞ በመግባት የለገጣፎን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ መሪነቱን አስፍቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንግዳው ቡድን አቄቂ ቃሊቲ የተሻለ በመንሳቀስ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ተደገጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቷል። በተለይም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ጉልላት ተሾመ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን ቢያልፈውም የለገጣፎ ለገዳዲ ተከላካይ ደርሶ ያዳናት አስቆጪ ነበረች። ባለሜዳዋቹ ከእረፍት መልስ በመልሱ ማጥቃት ያደረጉት እንቅስቃሴ እምብዛም የግብ እድል ለመፍጠር ባያስችላቸውም በ72ኛው ደቂቃ በሱፍቃድ ነጋሽ ከቆመ ኳስ አክርሮ የመታውን ኳስ የግብ ጠባቂው ስህተት ታክሎበት ሶስተኛ ግብ መሆን ችሏል። ጨዋታውም በለገጣፎ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወደ ወልዲያ ያመራው ሰበታ ከተማ ወልድያን 2-1 በማሸነፍ የመጀመርያውን ዙር በግብ ልዩነት በልጦ ቀዳሚ በመሆን አጠናቋል። በ23ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂያቸውን በቀይ ካርድ በማጣቸው ቀሪውን ረጅም ክፍለ ጊዜ በጎዶሎ የተጫወቱት ሰበታዎች በ13ኛው ደቂቃ ጫላ ዲሪባ ባስቆጠረው ገል ቀዳሚ ሲሆኑ ከዕረፍት መልስ ተስፋዬ ነጋሽ ወልዲያን አቻ ማድረግ ችሏል። በ83ኛው ደቂቃ ደግሞ ናትናኤል ጋንቹላ የሰበታን የማሸነፍያ ጎል አስቆጥሯል።

አክሱም ላይ አክሱም ከተማን የገጠመው ፌዴራል ፖሊስ 2-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በ4ኛው ደቂቃ አስማረ ምህረት እንዲሁም በ25ኛው ደቂቃ ቻላቸው ቤዛ ያስቆጠሯቸው ጎሎች እንግዳውን ቡድን ድል አስጨብጠዋል።

ወሎ ኮምቦልቻ ኢትዮ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ በ58ኛው ደቂቃ ነቢዩ አህመድ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1-0 ሲያሸንፍ ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማ አማራ ውሃ ስራን በ38ኛው ደቂቃ የጫላ ቡልቲ ጎል በተመሳሳይ 1-0 ረቷል። ደሴ ላይ ደሴ ከተማ ከ ገላን ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታው ደሴዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *