የአሰልጣኞች አስተያየት | መቐለ 70 እንደርታ 2-1 ጅማ አባ ጅፋር

ዛሬ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በመቐለ 70 እንደርታ እና ጅማ አባ ጅፋር መካከል ተደርጎ በባለሜዳዎቹ 2-1 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

” የዛሬው ድል ትልቅ ድል ነው ምክንያቱም ለሁለተኛው ዙር ስንቅ ነው የሚሆነን” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

ስለ ጨዋታው

” ዛሬ ቡድናችን ጥሩ ተጫውቷል ብዬ አላስብም። የሚያስፈልገንን ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ግን ጥሩ ነገር ነው። በእቅዳችን መሰረት የምንፈልገውን አግኝተናል። ይሁን እንጂ ከዕረፍት በፊት ጥሩ አልነበርንም ከዕረፍት በኃላ ግን ለማሻሻል ሞክረናል ፤ ባጠቃላይ ግን ስናየው ብዙ ተጫዋቾች ስለተጎዱብን ለማስተካከል ከብዶን ነበር ማሸነፋችን ግን ጥሩ ነው። ”

የዛሬው ድል ለቀጣይ ያለው ፋይዳ

” የዛሬ ድል ትልቅ ድል ነው ምክንያቱም ለሁለተኛው ዙር ስንቅ ነው የሚሆነን ፤ አንደኛ ነገር በሰፊ ነጥብ ነው እየመራን ያለነው ከሁለተኛው በአምስት ነጥብ ከሦስተኛው በሰባት ነጥብ መሆኑ የዛሬውን ድል ትርጉሙ ትልቅ ነው። ”

ስለ ቡድኑ የሁለተኛው ዙር ዕቅድ እና ስለዝውውር

” ያለውን ውጤት ማስቀጠል ነው ምንፈልገው። ሁለተኛው ዙር ከባድ ነው ምክንያቱም በዚህ ሰዓት ብዙ ጉዳቶች አሉብን ፤ የተጎዱት ተጫዋቾች ቶሎ ከተመለሱልን ጥሩ ነው። ሆኖም አብዛኞቹ ከበድ ያለ ጉዳት ነው ያላቸው። ሃይደር በቅርብ ሊመለስ ይችላል ፤ ከዛ ውጪ ግን ተጫዋቾች ለመጨመር ዕቅድ አለን ካሉን ተጫዋቾች ጨምረን ጥሩ ቡድን ይዘን እንመለሳለን። ”

“በየአራት ቀን መጫወታችን ጫና አብዝቶብናል” የሱፍ ዓሊ ጅማ አባ ጅፋር

ስለ ጨዋታው

” በዛሬው ጨዋታ ሁለታችንም ነፃ ሆነን ነው የተጫወትነው። ሆኖም ያገኘናቸው ዕድሎች ባለመጠቀማችን ውጤቱ እንዲህ ሆኗል። ”

ስለ ስታድየም ድባብ እና ጨዋታዎች መደራረባቸው

” አቀባበሉ እንደተለመደው ነው፤ የትም ቦታ ሄደን የምናወራለት ነው። አምናም ዘንድሮም አቀባበላቸው በጥሩ ነው። ይሄ እኛ የምንመሰክርለት ነው። ከዛ በተረፈ ግን በአራት ቀን በመጫወታችን ጫና በዝቶብናል ስብስባችንም አስራ ሦስት ነበር። በአራት ቀን ተጫዋቾች እየየጎዱ ነው ፤ ያላቸውን ነገር አውጥተው ነው እንደውም ይህን ውጤት የመጣው። ”

የቡድናቸው የቀጣይ ዕቅድ

” ጨዋታዎቻችንን ጨርሰናል ፤ ብዙ ክፍተቶች አሉብን። አዲስ የተጨመሩ ተጫዋቾችም አሉን። የተሻለ ተፎካካሪ ሆነን ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ነው እቅዳችን። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *