ሪፖርት | መቐለ ከተከታዮቹ ያለውን ልዩነት በማስፋት አንደኛውን ዙር አጠናቋል

መቐለ 70 እንደርታ በኦሴይ ማውሊ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ግቦች ታግዞ ስምንተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

ምዓም አናብስት ባለፈው ሳምንት ባህርዳር ከተማን ካሸነፈው ስብስባቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ አባ ጅፋሮች ባለፈው ሳምንት ከፋሲል ከነማ አቻ ከተለያየው ስብስብ አስቻለው ግርማ እና ይሁን እንደሻውን አስወጥተው በመስዑድ መሐመድ እና ቢስማርክ አፒያ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብዙም ሳቢ ባልነበረው እና በተደጋጋሚ የዳኛ ፊሽካ ታጅቦ የተካሄደው የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታ በአንፃራዊነት እንግዶቹ ጅማዎች ተሽለው የታዩበት እንዲሁም በርካታ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር። በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በዲዲየ ሌብሪ ጥረት የተፈጠሩ ሁለት ዕድሎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ ፤ በተለይም ራሱ ዲድዬ ለብሪ ከሩቅ መትቶ ለጥቂት የወጣችበት እንዲሁም ማማዱ ሲድቤ ከፍሊፕ ኢቮኖ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በጥሩ ብቃት ያወጣበት ይስተቀሳሉ። የመጀመርያው አጋማሽ አመዛኙ ደቂቃ ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ቻምፒዮኖቹ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ሙከራዎች ውጪም በቢስማርክ አፕያ ጥሩ ሙከራ አድርገው ነበር ፤ ቢስማርክ ሄኖክ ገምቴሳ ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ ሁኔታ ቢመታም ፍሊፕ ኦቮኖ በድንቅ ብቃት አድኗታል።

በጨዋታው ያሬድ ከበደ ፣ ኦሴይ ማውሊ እና አማኑኤል ገ\ሚካኤል በግል ከሚያደርጓቸው ጥረቶች ውጭ እንደ ቡድን በጥሩ ሁኔታ ማጥቃት ያልቻሉት መቐለዎች ምንም እንኳ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በሦስት አጋጣሚዎች ጥሩ የጎል መከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ዮናስ ገረመው ከቅጣት ምት አሻምቷት ስዩም ተስፋዬ ያልተጠቀመት ዕድል እና ያሬድ ከበደ ከርቀት መትቶ አዳማ ሲሶኮ ተደርቦ የመለሳት ኳስ ቡድኑ ከፈጠራቸው ዕድሎች የተሻሉ ነበሩ።

በጨዋታው የከድር ኸይረዲ እና አዳማ ሲሶኮን ጠንካራ ጥምረት አልፈው ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል ያልተጠጉት መቐለዎች በሠላሳ አንደኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል ፤ አማኑኤል ገ\ሚካኤል ከዮናስ ገረመው የተላከችለት ኳስ ከዳንኤል አጄይ ጋር አንድ ለ እንድ ተገናኝቶ መትቶ ግብ ጠባቂው ቢመልሰውም የተመለሰው ኳስ በድጋሜ መትቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ዲዲዬ ለብሬ በተሰለፈበት የግራ መስመር አዘንብለው ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት እንግዶቹ ጅማዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ በማማዱ ሲዲቤ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ አጥቂው ከመስመር መሬት ለመሬት ያሻገረለት ኳስ በጥሩ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።

እጅግ ጥሩ የፉክክር መንፈስ እና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ምንም እንኳን በርካታ የግብ ሙከራዎች ባያስተናግድም በብዙ መመዘኛዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ነበር። ባለሜዳዎቹ ተሽለው በታዩበት በዚህ አጋማሽ ባለሜዳቸው በተለመደው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እጅግ ብዙ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል ፤ በተለይም በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች የተፈጠሩት ዕድሎች በርካታ ነበሩ። ከነዚህም ዮናስ ገረመው ከቅጣት ምት ያደረጋት ሙከራ የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች።

በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የመቐለው ተከላካይ አሌክስ ተሰማ ከቡድን ጓደኛው አሚን ነስሩ ተጋጭቶ በጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ተቀይሮ በመውጣት ለተሻለ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል። ከተጋጣሚያቸው የተከላካይ ክፍል ጀርባ ያለው ክፍተት ያነጣጠሩ ረጃጅም ኳሶች እና ፈጣን የመስመር የማጥቃት ሽግግሮች ሲተገብሩ የተስተዋሉት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በመጨረሻዎቹ ሠላሳ ደቂቃዎች ተጭነው በመጫወት በርካታ ያለቀላቸው ዕድሎች ፈጥረዋል በተለይም ኦሴይ ማውሊ ከመስመር አሻምቷት ሚካኤል ደስታ በግንባሩ ገጭቷት ለጥቂት የወጣችው ሙከራ በመቐለዎች በኩል የምታስቆጭ ነበረች።

ኦሴይ ማውሊ በስልሳ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ እና አማኑኤል አንድ ሁለት ተቀባብለው ያሬድ ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ በኃላም የተጋጣሚን ግብ ክልል በመፈተሹ ያልቦዘኑት መቐለዎች በቢያድግልኝ ኤልያስ እና አማኑኤል ገ\ሚካኤል ሁለት ጥሩ ሙከራዎች አድርገድ ነበር። በተለይም አማኑኤል ገ\ሚካኤል በሚያደንቅ ብቃት ዳንኤል አጄይን እና ሁለት ተከላካዮች አልፎ መትቶ ከድር ኸይረዲን እጅግ በሚያስደንቅ ብቃት ከመስመር ያወጣው ኳስ ከታዩት ሙከራዎች እጅግ ለጎል የቀረበ ነበር።

ከዚህ ውጭ አማኑኤል ከዬናስ ገረመው የተሻገረችለት ኳስ አብርዶ መቶ ዳንኤል አጄይ በጥሩ ብቃት ያዳናት ኳስም ትጠቀሳለች። በመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች ጎል ፍለጋ ተጭነው የተጫወቱት ጅማዎች በበርካታ እጋጣሚዎች አቻ የመሆን ዕድል ቢያገኙም በጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው ፍሊፕ ኦቮኖን አልፈው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በተለይም ዲድየ ለብሬ ከሳጥኑ ጠርዝ መቷት ግብ ጠባቂው ከግቡ አፋፍ የመለሳት እና ዲድየር ሌብሬ በራሱ ጥረት ከመስመር አሻምቷት በሳጥን ነፃ አቋቋም የነበረው ቢስማርክ አፕያ በደረቱ ገጭቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት ጅማን በመጨረሻው ደቂቃዎች አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ውጤቱን ተከትሎ መቐለዎች ከተከታያቸው ሲዳማ ቡና የአምስት ነጥቦች ብልጫ ሲያስመዘግቡ ቻምፕዮኖቹ ደረጃቸው ለማሻሻል የነበራቸው ዕድል አምክነዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *