የሴካፋ ዋንጫ በቀጣዩ ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ይጀመራል፡፡ በርካታ ተጫዋቾችን ከምስራቅ አፍሪካ የሚያመጡት ክለቦቻችንም በሃገራችን ከሚስተናገደው ውድድር ተጫዋች ለመመልመል ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ክለቦቻችን በትክረት ሊመለከቷቸው የሚገቡ ተጫዋቾችን በተከታታይ ታቀርብልዎታለች፡፡ በዛሬው ፅሁፋችን ሳምንቱን በድንቅ አቋም ያሳለፈው የዩጋንዳው የመስመር አጥቂ ፋሩክ ሚያን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
በሃምሌ ወር 2006 ዓ.ም. የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለ2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ይረዳው ዘንድ በሉጎጎ በሚገኘው የፊሊፕ ኦሞንዲ ስታዲየም ከሲሼልስ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አደረገ። በዕለቱ ዩጋንዳ እንደ ቡድን ያሳየችው ደካማ አቋም መሃል ግን አንድ ወጣት ድንቅ ብቃቱን ያሳይ ነበር። ይህ አስደናቂ ተጫዋች በጨዋታው 27ተኛ ደቂቃ ላይ ሪቻርድ ካሳጋ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ በግንባር በመግጨት ግሩም ግብ አስቆጠረ። ዩጋንዳም 1-0 በሆነ ውጤት ጨዋታውን ማሸነፍ ቻለች። ሰርቢያዊው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሚሉቲን ሰርዶጄቪች (ሚቾ) ከጨዋታው በኋላ እንዲህ ሲሉ ተናገሩ።
“በጨዋታው የነበረው እንቅስቃሴ፣ ጨዋታ የማንበብ ችሎታው፣ በማጥቃት ሂደት ላይ የነበረው ተሳትፎ፣ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር የነበረው መናበብ ሲታይ ለረጅም ዓመታት የመጫወት ልምድ ያለው ተጫዋች እንጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃገሩን ወክሎ እየተጫወተ የሚገኝ የ18 ዓመት ታዳጊ አይመስልም ነበር። ”
እየተነጋገርን የምንገኘው ስለ ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን እና ቫይፐርስ ክለብ የመስመር አማካይ ፋሩክ ሚያ ነው።
ይህ ከሲሼልስ ጋር የተደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ለፋሩክ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል ጨዋታ ቢሆንም ከዚያ በፊት ብሔራዊ ቡድኑ ከሀገር ውስጥ ክለቦች ጋር ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች 3 ግቦችን በማስቆጠር ችሎታውን አሳይቶ ነበር። አሠልጣኝ ሚቾም ለወደፊቱ ብሔራዊ ቡድን መሠረት ሊሆን የሚችል ተጫዋች በእጃቸው እንደገባ ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም።
ፋሩክ ሚያ ማን ነው?
ፋሩክ ሚያ እ.ኤ.አ. በህዳር 26 1997 በካምፓላው ሙላጎ ሆስፒታል ነበር ይህቺን ዓለም የተቀላቀለው። የፋሩክ የእግርኳስ ህይወት የጀመረው በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኝ ቤተክርስቲያን እሁድ እሁድ ከጓደኞቹ ጋር በመጫወት ነበር። ከ8 ዓመቱ ጀምሮም የእግርኳስ ጓደኞች (Friends of Football) እና የካምፓላ ልጆች ሊግ (Kampala Kids League) በተባሉ የህፃናት ቡድኖች ውስጥ መጫወት ጀመረ።
የካምፓላ ልጆች ክለብ ለፋሩክ ሚያ የእግርኳስ ዕድገት ወሳኝ መሠረት ነበር። ቡድኑ በ2013 የኖርዌይ ዋንጫ የ16 ዓመት በታች እና የ19 ዓመት በታች ውድድሮች ሻምፒዮን ሲሆን በሁለቱም የዕድሜ እርከኖች ተሰልፎ ከመጫወቱም በላይ የሁለቱም ውድድሮች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ለመጨረስ ችሏል። በተለይ ከ19 ዓመት በታች ውድድር ላይ ያስቆጠራቸው 19 ግቦች የውድድሩ ሪከርድ ሆኖ ለመመዝገብ በቅቷል።
ፋሩክ ትምህርት ቤቱን ወክሎ በተሳተፈባቸው ውድድሮች ላይም ውጤታማ ከመሆን ያገደው ነገር አልነበረም። በዩጋንዳ ኮፓ ኮካኮላ ውድድር የኪቴንዴ ቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት (St Mary Kitende) ለ3 ተከታታይ ጊዜያት ሻምፒዮን ሲሆን የፋሩክ ሚና ቀላል አልነበረም። ቡድኑ በምስራቅ አፍሪካ የ2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የእግርኳስ ውድድር ላይም አሸናፊ ለመሆን ችሏል። በታህሳስ ወር 2006 ዓ.ም. ላይም የሚማርበት ክያምቦጎ ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ ዩንቨርስቲዎች ውድድር ዋንጫን ሲያነሳ ፋሩክ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው።
የክለብ እግርኳስ
የኪቴንዴ ቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት የእግርኳስ ቡድን በርካታ ተጫዋቾችን ለሃገሪቱ ሊግ ክለቦች እና ለብሔራዊ ቡድኑ በማቅረብ ትልቅ ታሪክ ቡድን ነው። ትልልቅ የዩጋንዳ ሱፐርሊግ ክለቦች ፋሩክን ለማግኘት ፉክክር ውስጥ ገብተው የነበሩ ቢሆንም ተጫዋቹ ግን የቋሚ ተሰላፊነትን ለማግኘት ሲል ወደ ቫይፐርስ ስፖርት ክለብ ለመግባት መርጧል። ፋሩክ የዩጋንዳን ትልቁ የክለብ እግርኳስ መድረክ መልመድ ቀላል ሆኖ አላገኘውም። ከፍተኛ ፍጥነት፣ የረጅም ኳስ እና የጉልበት ጨዋታ በሚታይበት ሊግ ውጤታማ ለመሆን ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበት ነበር። ፋሩክ በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ መገባደጃ ላይ ግን ቀድሞ የሚታወቅበትን ድንቅ የእግርኳስ ክህሎት ማሳየት ጀመረ።
የ2014/15 እ.ኤ.አ. የውድድር ዘመን ለፋሩክ በክለብ እግርኳስም ሆነ በብሔራዊ ቡድኑ ያለውን እምቅ ችሎታ አውጥቶ ያሳየበት ነበር። ክለቡ የዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን ሆኖ ያጠናቀቀበትን ውጤት ሲያስመዘግብ ፋሩክ ሚያ ደግሞ በውድድር ዘመኑ ባሳየው ብቃት የዓመቱ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን ደፋ።
ብሔራዊ ቡድን
ፋሩክ ሚያ በሲሼልሱ የወዳጅነት ጨዋታ በመጀመርያ ጨዋታው ግብ ካስቆጠረ በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች ቋሚ ተሰላፊነቱን አስከብሮ ቀጥሏል። ባጠቃላይ የሃገሩን ማልያ ለብሶ በተጫወተባቸው 19 ጨዋታዎች 9 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ግብ የማስቆጠር ችሎታው ደግሞ አሠልጣኝ ሚቾ እምነት እንዲጥሉበት አድርጓል። የፋሩክ 2ኛ ጎል ዩጋንዳ የማርያኖ ባሬቶን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካምፓላ ላይ 3-0 ባሸነፈችበት የወዳጅነት ጨዋታ የመጣ ነበር። ዩጋንዳ ናይጄሪያን በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት በአክዋ ኢቦም ስታዲየም 1-0 ስታሸንፍ ግብ አስቆጣሪው ልማደኛው ፋሩክ ሚያ ነበር። ባሳለፍነው ሳምንት በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን የቶጎ አቻውን በድምር ውጤት 4-0 ማሸነፍ ሲችል ፋሩክ ከግቦቹ 3ቱን (ከሜዳ ውጪ ያሸነፉበትን ግብ ጨምሮ) ማስቆጠር መቻሉ ተጫዋቹ ያለበትን ወቅታዊ አቋም የሚያሳየን ነው።
የፋሩክ ብቃቶች
ለሩዋንዳው የቻን ውድድር ሱዳንን በሰፊ ውጤት አሸንፎ ማለፍ የቻለውና ምዕራብ አፍሪካዊቷን ቶጎ በአሳማኝ ሁኔታ በመርታት የዓለም ዋንጫውን የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ የተቀላቀለው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ካለበት ወቅታዊ አቋም አንፃር የዘንድሮውን የሴካፋ ውድድር ለማንሳት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል። ቡድኑ በርካታ ጥሩ ችሎታ ያለቸው ተጫዋቾች ባለቤት ቢሆንም አጨዋወቱ የሚያጠነጥነው ግን በወጣቱ ፋሩክ ሚያ ዙሪያ ነው። ከኳስ ውጪ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች፣ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ያለው መናበብ፣ ያለው ቴክኒካዊ ብቃት እና የቆሙ ኳሶችን የመጠቀም ችሎታው ቡድኑ የቆመበት መሠረት ነው።
ይህ ሳምንት የፋሩክ የግብ ማስቆጠር ብቃት የታየበት ሳምንት ነው፡፡ ቶን 4-0 አሸንፈው ወደ አለም ዋንጫ ማጣርያ የምድብ ፍልሚያ መግባታቸውን ሲያረጋግጡ 3 ግቦች የተገኙት ከፋሩክ ሚያ ነው፡፡ ተጫዋቹ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከውስጥ የመውጣት እና ከተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍተት የመጠቀም ክህሎቱ መልካም ነው፡፡
በመጪው የጥር የዝውውር መስኮት ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድናቸውን ለማጠናከር ያሰቡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ይህንን ተጫዋች አትኩሮት ሰጥተው ቢመለከቱት ጥሩ ነው። የተጫዋቹ ስም ከወዲሁ ከትልልቆቹ የታንዛኒያ እና ኬንያ ክለቦች ጋር እየተያያዘ ሲሆን በሩዋንዳው የአፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና (ቻን) ላይ ተሰልፎ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የሚችል ከሆነ ደግሞ በመላው አፍሪካ ዕይታ ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው።
አሠልጣኝ ሚሉቲን ሰርዶጄቪች ‹‹ሚቾ›› ለፋሩክ ያላቸው ራዕይ ግን ከአፍሪካም ያለፈ እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
“ፋሩክ ሚያ ከሲሼልስ ጋር ከነበረው ጨዋታ ጀምሮ በችሎታው እያደገ የመጣ ተጫዋች ነው። ጠንክሮ መስራት ከቀጠለ ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ አልጠራጠርም። ከክለቡ ቫይፐርስ ጋር በመሆንም ወደፊት በታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች መጫወት እንዲችል እየሰራን እንገኛለን።”