ኮንጎ ሪፑብሊክ ከ ኢትዮጵያ – የአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ

በ2018 ሩሲያ ለምታስተናግደው የአለም ዋንጫ ለማለፍ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን በቅድመ ማጣሪያው በድምር ውጤት 3-1 አሸንፎ ወደ ቀጣዩ የቅድመ ማጣርያ ዙር ያለፈው የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ስብስብ ባሳለፍነው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከኮንጎ አቻው ጋር የመጀመሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታውን አድርጎ በሜዳው 4-3 በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ ሁለተኛውን የደርሶ መልስ ጨዋታውን ለማድረግ ትላንት ረፋዱ ላይ ወደ ብራዛቢል አቅንቷል፡፡

በቅርብ አመታት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ አዎንታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ያለችው ኮንጎ ሪፑብሊክ በመጀመርያው ጨዋታ በአፍሪካ ፈታኝ የሆነውን የሜዳ ውጪ ጨዋታ በድል በማጠናቀቅ ወደ ምድብ ማጣርያው አንድ እግሯን ማስገባት ችላለች፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው ባደረገው ጨዋታ ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ ተበልጦ የነበረ ሲሆን ቡድኑ ከመጀመሪያው ጨዋታ በተሻለ ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀው ይገመታል፡፡ በተቃራኒው የክላውድ ሌሮዋ ኮንጎ ከሜዳው ውጭ እንደዚህ አይነት ጣፋጭ ውጤት ማስመዝገቡ ለቡድኑ ትልቅ የራስ መተማመን እንደሚያዳብርለት መናገር ቀላል ነው፡፡

በመጀመሪያው ጨዋታ በየቦታው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ክፍተት ሲያሳጡት የነበረው የቀያዮቹ ሰይጣኖች ተጨዋቾች በተለይም 4-1 እስከመሩበት ጊዜ ከጫና ነፃ በመሆንና ተረጋግተው በመጫወት የቡድናችንን የቡድንም ሆነ የግለሰብ የአጨዋወት ደረጃ ፍንትው አድርገው አሳይተውናል፡፡

 

ወቅታዊ ሁኔታ

ቡድናችን ትላንት ወደ ብራዛቪል አቅንቶ ቀለል ያለ ልምምድ ያደረገ ሲሆን ይህ ፅሁፍ በሚዘጋጅበት ሰአት በሚጫወትበት ስታድየም ላይ ልምምድ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

 

ጉዳት እና ቅጣት

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለኮንጎው የመጀመርያ ጨዋታ መርጠዋቸው ከነበሩት ውስጥ 17 ተጫዋቾች እና ራምኬል ሎክን ጨምረው የወሰዱ ሲሆን በቅጣት የማይሰለፍ ተጫዋች የለም፡፡ በልምምድ ፣ የእርስ በእርስ ጨዋታ እና በኮንጎው ጨዋታ ወቅት ተቸግረው የተስተዋሉት አስቻለው ታመነ እና ሽመልስ በቀለ ለጨዋታው ላይሰለፉ የሚችሉበት እድል ይኖራል ተብሏል፡፡ አስቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከነማ ባደረገው ጨዋታ ከደረሰበት ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ማገገም እንዳልቻለ ታውቋል፡፡

 

ካለፈው ጨዋታ ሊኖሩ የሚችሉ ለውጦች

ራምኬል ሎክ ከእስር ተፈትቶ ወደ ኮንጎ በመጓዙ የአሰልጣኝ ዮሃንስ የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ይካተታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኮንጎው ጨዋታ ጠፍቶ የዋለው በረከት ይስሃቅን ተክቶ ሊሰለፍም ይችላል፡፡ ይህም ሳስቶ የነበረውን የመስመር አጨዋወት ሊያሻሽል ይችላል፡፡

ዋሊድ አታ ከአስቻለው ታመነ ቀድሞ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሊካተት ይችላል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ያልተሰለፈው ዋሊድ ከጉዞ ድካም አገግሞ ለጨዋታ ብቁ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቡድኑ ከሜዳ ውጪ እንደመጫወቱና የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ እንደመግባቱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የተደራጀ የአማካይ ክፍል እና በርካታ የማጥቃት ባህርይ ያላቸውን ተጫዋቾች ሊያሰልፉ ይችላሉ፡፡

 

የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው ያደረጋቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች

31/01/15 የአፍሪካ ዋንጫ – ኮንጎ (ብራዛቪል) 2-4 ኮንጎ (ኪንሳሻ)

14/06/15 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ – 1-1 ኬንያ

01/09/15 የወዳጅነት ጨዋታ – ኮንጎ 2-3 ጋና

13/10/15 የወዳጅነት ጨዋታ – ኮንጎ 2-1 ቤኒን

31/10/15 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ – ኮንጎ 0-1 ካሜሩን

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ያደረጋቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች

28/08/15 የወዳጅነት ጨዋታ – ሩዋንዳ 3-1 ኢትዮጵያ

05/09/15 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ – ሲሸልስ 1-1 ኢትዮጵያ

30/09/15 የወዳጅነት ጨዋታ – ቦትስዋና 2-3 ኢትዮጵያ

08/10/15 የአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ – ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ 1-0 ኢትዮጵያ

18/10/15 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ – ቡሩንዲ 2-0 ኢትዮጵያ

ጨዋታው 33 ሺህ ደጋፊዎችን መያዝ በሚችለውና የሰው ሰራሽ ሳር በተገጠመለት ስታዴ አልፎንሴ – ማሳምባ – ዴባቴ ስታዲየም ነገ ይደርጋል፡፡

ጨዋታውን የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከጎረቤት ሱዳን ናቸው፡፡ የመሀል ዳኛው ኤል ፋዲል ሙሀመድ ሲሆን ሁለቱ ረዳት ዳኞች ዋሊድ አህመድ እና ሙሀመድ አብደላ ኢብራሂም እዲሁም አራተኛ ዳኛው ሙታዝ ካይራላ ናቸው፡፡

ይህንን የደርሶ መልስ ጨዋታ በድምር ውጤት የሚያሸንፍ ቡድን ሩሲያ በ2018 ለምታስተናግደው የአለም ዋንጫ ለማለፍ ወደሚደረገው የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ የሚያልፍ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *