ዓይናለም ኃይለ ዳግም ወደ ሜዳ ሊመለስ ነው

የፋሲል ከነማ ተከላካይ ዓይናለም ኃይለ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ዐፄዎችን በመቀላቀል ልምምድ ሊጀምር ነው።

ዓይናለም በ2009 መጨረሻ ላይ ከደደቢት ጋር በመለያየት ፋሲል ከነማን ከተቀላቀለ በኋላ በ2010 የውድድር ዘመን በድሬደዋ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከድሬደዋ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ነበር ጉዳት ያጋጠመው። ለወራት በሀገር ውስጥ ህክምና ሲያደርግ ቢቆይም ምንም ለውጥ ሊያገኝ ባለመቻሉ ለተሻለ ህክምና ወደ ታይላድ ባንኮክ በማቅናት የተሳካ ህክምና በማድረግ ተመልሷል።

በጉዳት እስከራቀበት ጊዜ ድረስ ጎሎችን በማስቆጠርና በጠንካራ መከላከል የዐፄዎቹ የኋላ ደጀንነቱን ያሳየው ዓይናለም ኃይለ ከወራቶች ጉዳት በኋላ በፋሲል ማልያ ከሁለተኛው አጋማሽ የውድድር ዘመን ጀምሮ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ለማወቅ ችለናል።

ዓይናለም በጉዳት ስለቆየባቸው ወራቶች እና በቀጣይ ከፋሲል ከነማ ጋር ስለሚያስበው ለሶከር ኢትዮጵያ እንዲህ ብሏል። ” በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ድሬዳዋ በደረሰብኝ ጉዳት ከሜዳ በአንቡላስ ነበር ወደ ሆስፒታል ያመራሁት። ከዛም አዲስ አበባ መጥቼ ጉዳትህ እረፍት ነው የሚፈልገው ብለውኝ አራት ወር ባርፍበትም ምንም ለውጥ ላገኝ ባለመቻሌ ወደ ታይላንድ ሄጄ ጥሩ ህክምና ተከታተትዬ ተመልሻለሁ። አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለው፤ ከሚቀጣለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ጎንደር በማቅናት ከቡድኔ ጋር ተቀላቅዬ ልምምድ እጀምራለሁ። በፍጥነትም ወደ ጨዋታ እመለሳለው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።” ብሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *