ዋሊድ አታ ወደ እግር ኳስ ተመለሰ

ባለፈው ዓመት ከእግርኳስ ተጫዋችነት ራሱን ማግለሉን አስታውቆ የነበረው የ33 ዓመቱ ተከላካይ ዋሊድ አታ በስዊድን አራተኛ ዲቪዝዮን ለሚወዳደረው ሂታርፕ አይ ኬ ፌርማውን በማኖር ወደ እግርኳስ ተመለሰ።

በ2007 በአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ጥሪ ተደርጎለት በ4 ጨዋታዎች ላይ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተጫወተው እና በእግር ኳስ ህይወቱ ለአስራ ሁለት ክለቦች የተጫወተው ዋሊድ አታ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከሳዑዲ ዓረብያው ክለብ አል ካሊጅ ከተለያየ በኋላ ራሱን ከእግር ኳስ እንዳገለለ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም ከስድስት ወራት ቆይታ በኃላ ዳግም ወደ እግር ኳስ ተመልሷል።

ዋሊድ አታ ከአዲሱ ክለቡ ሂታርፕ ለምን ያህል ግዜ ለመቆየት እንደተስማማ አልተገለፀም። ዳይናሞ ዛግሬቭ እና ለቱርኩ ጊንሲልበርጊ ጨምሮ ለበርካታ ክለቦች የተጫወተው አንጋፋው ተከላካይ 84 ቡድኖች በስድስት ምድብ ተደልድለው በሚሳተፉበት ሊግ በቅርቡ መጫወት ይጀምራል።

ዋሊድ አታ ወደ ክለቡ መቀላቀሉን ተከትሎ ከቢንያም በላይ እና የሱፍ ሳላህ ቀጥሎ በስዊድን ሃገር የሚጫወቱ ኢትያጵያውያን ወደ ሶስት ጨምሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *