ወላይታ ድቻ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በቅርቡ አሸናፊ በቀለን አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው ወላይታ ድቻ አንጋፋው ተከላካይ ደጉ ደበበ እና የቀድሞ አጥቂው አላዛር ፋሲካን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ ካሳለፈው ድንቅ 14 ዓመታት በኋላ ባለፈው ዓመት ከክለቡ ጋር የተለያየው ደጉ ደበበ ያለፉትን ወራት ከእግርኳስ ርቆ የቆየ ሲሆን በቅርቡ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ከጥቂት እረፍት በኋላ ወደ እግር ኳስ እንደሚመለስ ገልጾ እንደነበር የሚታወስ ነው። የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን አምበል የአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜ በወላይታ ድቻ ካሳለፈ በኋላ ወደ ክለቡ በይፋ ተቀላቅሏል፡፡


ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው በክለቡ ታሪክ ስመጥር ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አጥቂው አላዛር ፋሲካ ነው። ወላይታ ድቻ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው የቀድሞው የክለቡ አምበል እና አጥቂ በ2010 ጅማሮ ክለቡን በመልቀቅ ወደ አዳማ ከተማ አምርቶ የነበረ ቢሆንም በክለቡ ብዙም የመሰለፍ ዕድል ባለማግኘቱ በዛው ዓመት ግማሽ ላይ ወደ ሀዋሳ ከተማ በማምራት ጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ተጫዋቹ በክለቡ እንደ አዳማው ሁሉ የተሳኩ ጊዜያት በሀዋሳ ማሳለፍ ሳይችል ቀሪ ውል እያለው ከክለቡ በመለያየት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ሶዶ ከተማ አምርቶ ያለፉትን ስድስት ወራት ሲጫወት ከቆየ በኋላ ዳግም ወደ ቀድሞው ክለቡ የሚመልሰውን ዝውውር ማጠናቀቅ ችሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *