ቻን 2020 | ካፍ የኢትዮጵያ ጉብኝቱን ትላንት አጠናቀቀ

በ2020 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) አስተናጋጅ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት ቀናት በካፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች የስታዲየምቿ ዝግጅት ተገምግሟል።

ይህን ውድድር ያስተናግዳሉ ተብለው የተለዩትና ሙሉ ለሙሉ ተገንብተው መጠናቀቅ ያልቻሉት የሀዋሳ፣ መቐለ፣ ባህርዳር እና የአደይ አበባ ስታዲየሞችን ባሳለፍነው ዓመት ከካፍ በተላኩ ባለሙያዎች አማካኝነት በመዟዟር የተጎበኙ ሲሆን በዚህ ሳምንትም የመጨረሻው የግምገማ ምዕራፍ ተካሂዷል። የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ሊሆድጋር ቴንጋ እና ሞሰስ ማጎጎ፣ የካፍ የክለቦች ፍቃድ ሰጪ ኃላፊ አህመድ ሀራዝ እና ሁለት የሚዲያ ባለሙያዎች ሐሙስ ወደ አዲስ አበባ ከገቡ በኃላ ዓርብ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጉብኝታቸውን በማድረግ ነበር የግምገማ ጅማሮ ያደረጉት።

በመቀጠል ቅዳሜ ወደ መቐለ በማምራት የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየምን በመጎብኘት ግምገማ አድርገዋል። የመጫወቻ ሜዳውን እንዲሁም በስታዲየሙ ቅጥር ጊቢ የተሰራውን የመለማመጃ ሜዳ እና የመቐለ ዩኒቨርሲቲን ስታድየም የጎበኙ ሲሆን በተለይ የዓለም አቀፉን ስታድየም ውስጣዊ እና ውጫዊ አካል በመጎብኘት በሀዋሳ ስታዲየም የተገጠመው መብራት በመቐለ አለመከናወኑን እንደ ጉድለት ማንሳታቸው ታውቋል።

ዕሁድ የሶስተኛ ጉብኝታቸው መዳረሻን ባህር ዳር በማድረግ ዓለም አቀፍ ስታድየም፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ (ፔዳ ጊቢ)፣ የአፄ ቴዎድሮስ ስታድየም ከመለማመጃ ሜዳው ጋር ተመልክተዋል። ትላንት ከሰዓት ደግሞ በግንባታ ላይ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየምን ከተመለከቱ በኋላ የሚጠናቀቅበትን ጊዜ አስመልክቶ ጥያቄ አቅርበዋል። ለልምምድ ያገለግላሉ የተባሉትን በወጣቶች አካዳሚ ያሉ ሁለት የመለማመጃ ስፍራን ጨምሮ አንጋፋውን የአዲስ አበባ ስታዲየም የተመለከቱ ሲሆን አንድ የመለማመጃ ሜዳ ግን በቶሎ መሰራት እንዳለበት ለፌዴሬሽኑ ማሳሰባቸው ተነግሯል፡፡ ያለፍትን አምስት ቀናት የቻን 2020 የዝግጅት ግምገማን በማጠናቀቅም ትላንት ምሽት የተመለሱ ሲሆን ልዑኩ በቀጣይ ሳምንት የግምገማውን ውጤት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን እና ለሀገሪቱ መንግስት እንደሚልክ ተሰምቷል።

ረጅም የግንባታ ዓመታት የወሰዱት እና እስካሁን ሙሉ ለሙሉ ያልተጠናቀቁ በርካታ ስታድየሞች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የቻን ውድድርን ለማካሄድ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ በቀረበት በዚህ ወቅት ከሚመለከታቸው አካላት ስለ መስተንግዶው ቅድመ ዝግጅት እና እስካሁን እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች ይፋዊ መረጃ እየተሰጠ የማይገኝ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ መሟላት ከሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ የሆነው የስታድየም ቅድመ ሁኔታዎች (ደረጃውን የጠበቀ የመጫወቻ ሳር፣ የተጠባባቂ ተጫዋቾች እና የቡድን አመራሮች መቀመጫ፣ ፓውዛ፣ በስታድየሙ የተለያዩ ክፍሎች የሚገጠሙ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች፣ በቂ የመልበሻ ክፍል፣ የሚዲያዎች እና የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል፣ በቂ መፀዳጃ ክፍሎች፣ በአንድ ከተማ እስከ አራት የልምምድ ሜዳ) እና የመሳሰሉትን በቀሪዎቹ ወራት የማሟላት ኃላፊነት ይጠበቅባታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *