ብሄራዊ ቡድናችን በሀዋሳ ልምምዱን ሰርቷል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ ቀትር ላይ ሀዋሳ ገብቷል፡፡ ቡድኑ በከተማው ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን አመሻሹ ላይም በሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ ልምምድ ሰርቷል፡፡

ወደ ሀዋሳ ከተጓዘው ቡድን መካከል ታከለ አለማየሁ እና ምንይሉ ወንድሙ የተቀነሱ ሲሆን ታሪክ ጌትነት ከቡድኑ ጋር አብሮ አልተጓዘም፡፡ ነገር ግን ነገ ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ቡድኑን ሊቀላቀል ይችላል ተብሏል፡፡

በዛሬው ቀለል ያለ የልምምድ ፕሮግራም ባለፈው ጨዋታ ያልተሰለፈው ስዩም ተስፋዬ ልምምድ ሲሰራ በረከት ይስሃቅ እና ሳላዲን በርጊቾ ግን ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ልምምድ አልሰሩም፡፡

በሩዋንዳው ጨዋታ አምበል ሆኖ ተሰልፎ በጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ተቀይሮ የወው ሳለዲን በርጊቾ እና በተመሳሳ በቅዳሜው ጨዋታ በቁርጭምጭሚቱ ላይ ጉዳት ያስተናገደው በረከት ይስሃቅ ረቡእ ከሶማልያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ የመድረሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ ሁለቱ ተጫዋቾች ካልተሰለፉ እንዲሁም ተደራራቢ ጨዋታ በማድረጉ እረፍት ተሰጥቶት የነበረው ስዩም ተስፋዬ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ከተመለሰ ቡድኑ ለውጦች አስተናግዶ ሶማልያን ይገጥማል፡፡

በሀዋሳ ሳውዝ ስታር ሆቴል ያረፉት ዋልያዎቹ በነገው እለት ጠዋት ቀጣይ ልምምዳቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *