ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

የነገው የትግራይ ስታድየም ጨዋታ ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት ነው።

የሊጉ መሪዎች ነገ 09፡00 ላይ ወልዋሎ ዓ/ዩን የሚያስተናግዱበት ተጠባቂ ጨዋታ በትግራይ ስታድየም ይደረጋል። አስረኛ ተከታታይ ድላቸውን ያስመዘገቡት መቐለዎች የተጨዋቾች መለዋወጥም ከጉዟቸው የሚገታቸው አልሆነም። የያሬድ እና አማኑኤልን የፊት መስመር ጥምረት ባልተጠቀሙበት የደደቢቱ ጨዋታም የ4-1 ድል ማስመዝገብ ችለዋል። ሊጉን ከመምራት ባለፈም ቡድኑ ካስመዘገባቸው ድሎች ያካበተው በራስ መተማመን ለነገውም ጨዋታ ስንቅ እንደሚሆነው መገመት ይቻላል። መቐለ 70 እንደርታ አሞስ አቼምፖንግን በጉዳት ፊሊፕ ኦቮኖን በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ምክንያት የማይጠቀም ሲሆን ፤ ከጉዳት ተመልሰው ልምምድ የጀመሩት አሸናፊ ሃፍቱ ፣ ያሬድ ከበደ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ስብስቡ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገው ድል ያስመዘገቡት ወልዋሎዎች ወደ ሊጉ ወገብ ከፍ ማለት ችለዋል። ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻሉም ወደ አምስተኛነት የመጠጋት ዕድል ይኖራቸዋል። በቢጫ ለባሾቹ በከል አስራት መገርሳ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን ብርሀኑ ቦጋለ ደግሞ በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ምክንያት የማይሰለፍ ይሆናል።

የእርሰ በእርስ ግኑኝነት እና እውነታዎች

– 2005 ላይ ወልዋሎ ብሔራዊ ሊጉን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ቡድኖቹ በ13 ጨዋታዎች ሲገናኙ መቐለ ሦስቴ ወልዋሎ ደግሞ አንዴ ድል የቀናቸው ሲሆን ቀሪዎቹን ዘጠኝ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። በ12ቱ ጨዋታዎች መቐለ 70 እንደርታ 11 ግቦች እንዲሁም ወልዋሎ 8 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– እስካሁን ትግራይ ስታድየም ላይ መቀመጫቸውን እዛው ካደረጉት ክለቦች ጋር ሦስቴ የተገናኘው መቐለ ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል። ወልዋሎ ደግሞ በነገ ተጋጣሚው የተሸነፈ ሲሆን ደደቢትን ደግሞ ማሸነፍ ችሏል።

ዳኛ

– በዚህ ጨዋታ ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ በመሀል ዳኝነት የምንመለከተው ብርሀኑ መኩሪያ እስካሁን ስምንት የቢጫ ካርዶችን መዞ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ አንድ ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ቡጫ ካርድ ከሜዳ አስወጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ሶፎኒያስ ሰይፈ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – ያሬድ ሀሰን

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ

ሐይደር ሸረፋ – ዮናስ ገረመው – ያሬድ ብርሀኑ

ኦሰይ ማውሊ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-2-3-1)

አብዱላዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – ቢኒያም ሲራጅ – በረከት ተሰማ – ሰመረ ካህሳይ

ብርሃኑ አሻሞ – አማኑኤል ጎበና

ኤፍሬም አሻሞ – ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – አብዱርሀማን ፉሴይኒ

ሪችሞንድ አዶንጎ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *