ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ደቡብ ፖሊስ

ነገ በብቸኝነት የሚደረገው የደደቢት እና ደቡብ ፖሊስ ጨዋታን በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

በትግራይ ስታድየም 09፡00 ላይ በሚደረገው ጨዋታ ውጤቱን ማሻሻል ያልቻለው ደደቢት አስገራሚ ለውጥ ላይ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስን ያስተናግዳል። አራት ነጥቦች ላይ እንደቆሙ የቀሩት ደደቢቶች ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበራቸው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ የተላለፈ ቢሆንም ከዚያ አስቀድሞ ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎችን ተሸንፈዋል። ታደሰ አብርሃን ዛሬ በምክትል አሰልጣኝነት የሾሙት ሰማያዊዎቹ ከበላያቸው ካለው ስሑል ሽረ ጋር ብቻ በ 11 ነጥብ ልዩነት በመቀመጣቸው በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው እጅግ እየመነመነም ይገኛል። ውጤት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ በሚጠበቅበት የነገ ጨዋታ ተስፋ የሚሆናቸው ጉዳይ አዳዲስ ፈራሚዎቻቸውን ለመጠቀም የሚችሉ መሆኑ ነው። በዚህም ቅጣትም ጉዳትም የሌለበት ቡድኑ ከመቐለ በነበረው ጨዋታ በስራ ፍቃድ ምክንያት እና በሌሎች ያላለቁ የወረቀት ስራዎች ያልተሰለፉት ፉሴይኒ ኑሁ ፣ ሮበን ኦባማ ፣ አንቶንዮ አቡዋላ እና ኪሩቤል ኃይሉን መጠቅም ይችላል።

የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ደቡብ ፖሊስ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ እና ከወራጅ ቀጠናው በግብ ልዩነት ከፍ በማለት ነው ወደ መቐለ ያቀናው። ድሎቹን ተከትሎ በራስ የመተማመን መንፈሱ ፍፁም ተለውጦ እየታየ የሚገኘው ቡድኑ ሁለቱን ጨዋታዎች ከሜዳ ውጪ ማሸነፉ ደግሞ ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ነው። በነገውም ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይዞ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ሲጠበቅ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ማግኘት አለመቸገሩ እና የተረጋጋ የመከላከል ሽግግሩ ልዩነት ሊፈጥሩለት እንደሚችሉ ይታሰባል። ሆኖም የየተሻ ግዛው አለመኖር በቡድኑ የግራ ወገን የሚኖረውን የማጥቃት ሂደት ባለፉት ጨዋታዎች ከተመለከትነው የፊት ሦስትዮሽ ጥምረት ይየሰመረ ውህደት አንፃር ክፍተት ሊፈጥርበት ይችላል። ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ያጡትን ተከላካይ አበባው ቡታቆ በተጨማሪ የተሻ ግዛውን በህመም ኤርሚያስ በላይን ደግሞ በጉዳት የማይጠቀሙ ይሆናል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ደደቢት ወደ ሊጉ በመጣበት እና ደቡብ ፖሊስ በወረደበት የ2002 የውድድር ዓመት ደደቢት የ3-0 እና የ2-0 ድሎችን ሲያሳካ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ዘንድሮ የተገናኙበት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ደግሞ በደቡብ ፖሊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

– በትግራይ ስታድየም እስካሁን ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት ከአንድ ድል እና ለአንድ የአቻ ውጤት ውጪ በተቀሩት ሽንፈት አስተናግዷል።

– ከሰባት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በአራቱ ሽንፈት የገጠመው ደቡብ ፖሊስ ሁለቴ አሸንፎ ሁለቴ ደግሞ ነጥብ በመጋራት ተመልሷል። ቡድኑ ያሳካቸው ሁለቱ ድሎች በመጨረሻዎቹ ሁለት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች የተገኙ ነበሩ።

ዳኛ

– እስካሁን በአራት ጨዋታዎች ምንም ቀይ ካርድ ያላስመለከተው አዳነ ወርቁ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ ሁለቱን ቡድኖች አንድ አንድ ጊዜ የዳኘ ሲሆን በጥቅሉ በአራቱ ጨዋታዎች 18 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – አንቶንዮ አቡዋላ – ኤፍሬም ጌታቸው – ሄኖክ መርሹ

የዓብስራ ተስፋዬ – ኃይሉ ገብረየሱስ

ሮበን ኦባማ – ዓለምአንተ ካሳ – አቤል እንዳለ

ፉሴይኒ ኑሁ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ሐብቴ ከድር

አናጋው ባደግ– ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሐመድ – ዘሪሁን አንሼቦ

ዘላለም ኢሳይያስ – ዮናስ በርታ – ብሩክ አየለ

ብርሀኑ በቀለ – ሄኖክ አየለ – በረከት ይስሀቅ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *