ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ስሑል ሽረ

በአዳማ እና ሽረ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች ልናነሳ ወደናል።

የአዳማው አበበ ቢቂላ ስታድየም ነገ 09፡00 ላይ አዳማ ከተማን ከስሑል ሽረ የሚያገናኘውን የ18ኛ ሳምንት ጨዋታ ያስተናግዳል። በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1-0 ሽንፈት የደረሰበት አዳማ ከተማ ከፉክክሩ በእጅጉ ርቆ በሰንጠሩዡ ወገብ ላይ ይገኛል። አካሄዱም ያለፉትን አመታት ደረጃውን ይዞ ለመጨረስም ጭምር እንዳይቸገር ያሰጋዋል። አዳማ እምብዛም ግብ የማይቆጠርበት ዓይነት ቡድን ቢሆንም የማጥቃት አማራጮቹ ተገማች መሆን በቀላሉ ግቦችን እንዳያገኝ ያደረገው ይመስላል። በዚህ ረገድ በነገው ጨዋታ የቡድኑ የፈጠራ ምንጭ የከነዓን ማርክነህ ከኦሉምፒክ ቡድኑ መመለስ ከመስመር ለሚነሳው በረከት ደስታ እና ለፊት አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ ጥሩ አማራጮች እንደሚፈጥር ይጠበቃል። አዳማ በጊዮርጊሱ ጨዋታ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ያጣው የመሀል ተከላካዩ ምኞት ደበበን ጨምሮ የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ቡልቻ ሹራ እና አንዳርጋቸው ይላቅን የማይጠቀም ሲሆን ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ከብሔራዊ ቡድን ጥሪ መልስ ቡድኑን ተቀላቅሏል።

15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች ከወራጅ ቀጠናው መውጣት የሚያስችላቸው ነጥብ ፍለጋ ወደ አዳማ አምርተዋል። ሳምንት በባህር ዳር ላይ ያስኩት ድል ከተከታዮቻቸው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ በማድረጉ በሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን የመለሰ ሆኖ አልፏል።በሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀው የነበሩት ሽረዎች ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ማሳካታቸው የአዕምሮ ጥንካሬያቸውን የሚያጎለብት ስኬት ነው። ያም ቢሆን በነገው ጨዋታ ጥንቃቄን ምርጫው ያደረገ እና የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም ጥረት የሚያደርግ ቡድን ይዞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ከወገብ በላይ በውጪ ሀገር ዜጎች የተዋቀረ መሆኑ ፍጥነት እና ጉልበት ለሚፈልገው መልሶ ማጥቃት ጥሩ ዕድል የሚፈጥርለትም ይመስላል። ይህም አካሄድ ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉ ቡድኖችን ማስከፈት ሲቸግረው ለሚችለው ተጋጥሚው ፈታኝ ሊያደርገው ይችላል። በጨዋታው ስሑል ሽረዎች ከቢስማርክ አፒያ መሰለፍ አጠራጣሪነት ውጪ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነ ቡድን ይዘው ይቀርባሉ።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሽረ ላይ ሁለቱ ቡድኖች የተገናኙበት የመጀመሪያ የሊጉ የእርስ በርስ ግንኙነታቸው ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር። 

–  አዳማ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት እና ሦስት የአቻ ውጤትን ሲያስመዘግብ አራት ጨዋታዎችን በድል መወጣት ችሏል። 

– ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ ስምንት ጨዋታዎችን ሲያደርግ በአንድ ድል እና ነሁለት የአቻ ውጤቶች አምስት ነጥቦችን ሲያሳካ አምስት ሽንፈቶች ገጥመውታል። 

ዳኛ

– ጨዋታው ለተካልኝ ለማ የዓመቱ ስምንተኛ ጨዋታው ይሆናል። አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው እና ሁለት ተጫዋቾችን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ያስወጣው ተካልኝ 22 የማስጠንቀቂያ ካርዶች መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱሉይማን ሰሚድ – ቴዎድሮስ በቀለ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

 አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ 

ኤፍሬም ዘካርያስ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዮናስ ግርማይ  – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ረመዳን ዮሴፍ

አሳሪ አልመሐዲ– ደሳለኝ ደበሽ

ሳሊፍ ፎፎና – ያስር ሙገርዋ – ቢስማርክ ኦፖንግ

ቢስማርክ አፒያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *