ሪፖርት | የመድሃኔ ብርሃኔ ብቸኛ ግብ ሰማያዊዎቹን ጣፋኝ ድል አቀዳጅታለች

ዛሬ በመቐለ በተደረገ ብቸኛ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ደደቢት ደቡብ ፖሊስን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል ሲያስመዘግብ ነጥቡንም ወደ ሰባት ከፍ አድርጓል።

በዝናብ ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች በ16ኛው ሳምንት በመቐለ ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው አብዱልረሺድ ማታውኪል ፣ አሸናፊ እንዳለ ፣ መድሃኔ ታደሰ ፣ አቤል እንዳለ እና አብዱላዚዝ ዳውድን በማስወጣት ሙሴ ዮሐንስ፣ አንቶንዮ አቡዋላ፣ ዳግማዊ ዓባይ፣ ፉሴይኒ ኑሁ እና የዓብስራ ተስፋዬ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ እንግዶቹ ደቡብ ፖሊሶችም ባለፈው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈው ስብስባቸው አበባው ቡታቆ፣ ኪዳኔ አሰፋ፣ የተሻ ግዛው እና በኃይሉ ወገኔ በማስወጣት በዘሪሁን አንሸቦ፣ ብሩክ አየለ፣ ሄኖክ አየለ እና ብርሃኑ በቀለ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብዙም ንፁህ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት የመጀመርያው አጋማሽ የሁለቱም ጨዋታ በብዙ መለኪያዎች የሰማያዊዎቹን ብልጫ የታየበት ነበር። መድሃኔ ብርሃኔ ከመስመር በጥሩ ሁኔታ አሻምቷት ፉሴይኒ ኑሁ በግንባር ገጭቶ ባደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ሰማያዊዎቹ ግብ ለማስቆጠር ብዙ ግዜ አልፈጀባቸውም። 7ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምአንተ ካሳ ከመስመር ያሻገራት ኳስ ሐብቴ ከድር ሲመልሳት በግሉ ጥሩ ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ተስፈኛው መድሃኔ ብርሃኔ የተመለሰችው ኳስ ተጠቅሞ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ደደቢቶት እንደወሰዱት ብልጫ በርካታ ዕድሎች ባይፈጥሩም በመጀመርያው አጋማሽ ከጥልቀት እየተነሱ በማጥቃቱ ቁልፍ ሚና በነበራቸው ሁለቱ የመስመር ተጫዋቾች እንዳለ ከበደ እና መድሃኔ ብርሃኔ አማካኝነት በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም መድሃኔ ከመስመር አሻግሯት ፉሴይኒ ኑሁ አክርሮ መትቶ ሐብቴ ከድር የመለሳት እና እንዳለ ከበደ ፉሴይኒ ኑሁ ያሻገራት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ጥሩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተወሰነ መልኩ ማንሰራራት ችለው የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች ከሰላሳኛው ደቂቃ በኃላ የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ብሩክ አየለ ከርቀት ካደረጋት ሙከራ ውጭ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ገብተው ያደረጉት ሙከራ አልነበረም። በአንፃሩ ደደቢቶች በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ደቂቃ በናይጀርያዊው አንቶንዮ አቡዋላ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም ሐብቴ ከድር እጅግ በሚያስደንቅ ብቃት ወደ ውጭ አውጥቷታል።

በርካታ የሜዳ ላይ ጥፋቶች እንዲሁም ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ደቡብ ፖሊሶች ጫና ፈጥረው ደደቢቶች ደግሞ ጥንቃቄ በመምረጥ የተንቀሳቀሱበት ነበር። በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ደደቢቶች ሶስት ያለቀላቸው ሙከራዎች ቢያደርጉም ሶስቱም በተመሳሳይ በሐብቴ ከድር ድንቅ ብቃት መክነዋል። በተለይም ፉሴይኒ ኑሁ እና አለምአንተ ካሳ ከቅጣት ምት ያደረጓቸው ሙከራዎች የሰማያዊዎቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ነበር።

በርካታ የሜዳ ላይ ያልተገቡ አጨዋወቶች በበዙበት የመጨረሻዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ደቡብ ፖሊሶች እጅግ ጫና ፈጥረው ቢጫወቱም ዮናስ በርታ ቢንያም አድማሱ ያሻገረመት ግሩም ኳስ ተጠቅሞ ካደረጋት ወርቃማ ዕድል ውጭ ይህ ነው የሚባል ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

በመጨረሻ ደቂቃዎች የደቡብ ፖሊስ አሰልጣኞች ቡድን የኳስ መላሾቹ ኳስ ለመመለስ ዘለግ ያለ ግዜ እየወሰዱ ነው በማለት ተቃውሟቸው ሲያሰሙ ታይተዋል።

ውጤቱ በዚ መጠናቀቁ ተከትሎ ደደቢቶች በዚህ ዓመት ሁለተኛው ድላቸው ሲያስመዘግቡ ደቡብ ፖሊሶችም ከአራት ተከታታይ ድል በኋላ ጉዟቸው ተገቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *