ከፍተኛ ሊግ | አርባምንጭ እና ኢኮስኮ ሲያሸንፉ ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ጥሏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ እየተካሄዱ ይገኛሉ። በምድብ ለ 3፣ በምድብ ሐ ደግሞ 5 ጨዋታዎች በዕለተ እሁድ ተከናውነዋል።

ምድብ ለ

በአዲስ አበባ ኦሜድላ ሜዳ ላይ የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ እና ድሬዳዋ ፖሊስ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ በብዙ መለኪያዎች የባለሜዳው አዲስ አበባ ብልጫ የታየበት ሲሆን በ10ኛው ደቂቃ ሙሀጅር መኪ ከርቀት አክርሮ በመታት ኳስ በግቡ አናት ወደላይ በመውጣት የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ አድርገዋል። ኳስ ከግብ ክልል ጀምሮ በመመስረት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉት የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በተደጋጋሚ የግብ እድል ቢፈጥሩም የድሬዳዎ ግብ ጠባቂ ሲያድንባቸው ታይቷል። ሆኖም በ27ኛው ደቂቃ ላይ ኢብሳ በፍቃዱ በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ በአግባቡ በመቆጣጠር በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ለነበረው እሱባለሁ ሙሉጌታ ወደ ኋላ መልሶ ሲያቀብለው እሱባለሁ ለሳዲቅ በሁለት ተከላካዮች መሐል ያሳለፈለትን ኳስ ሳዲቅ ሲቾ በግሩም ሁኔታ ወደግብነት ለውጦታል።

ከግብ መቆጠር በኋላ በድጋሚ በኢብሳ በፍቃዱ በግንባር የገጫት ኳስ በግቡ የግራ አግዳሚ የወጣችበት እድል አስቆጭ ነበረች። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተወሰነ መልኩ ማንሰራራት ችለው የነበሩት ድሬዳዎ ፖሊሶች ኳሱን ይዞ ለመጫወት ሙከራ ቢያደረጉም ወደ ተጋጣሚያቸው ሶስተኛ የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ይቆራረጥ የነበር። በ38ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ብርሃኑ በቅጣት ያሻማውን ኳስ ዘርዓይ ገብረስላሴ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው ያዳነበት የግብ እድልም ብቸኛ የመጀመርያ አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

በርካታ የሜዳ ላይ ጥፋቶች፣ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲሁም የጠራ የግብ እድል በመፍጠር እንግዶቹ ተሽለው በታዩበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ድሬዳዋ ፖሊሶች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ አዲስ አበባዎች ደግሞ ጥንቃቄ በመምረጥ የተንቀሳቀሱበት ነበር። በድሬ በኩል በ49ኛው ደቂቃ አቤል ብርሃኑ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ51ኛው ደቂቃ እስጢፋኖስ ብርሃኑ ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች።

ጨዋታው ከደቂቃ ደቂቃ በተሻገረ ቁጥር እየተቀዛቀዙ የነበሩት አዲስ አበባዎች ረዘም ላለ ደቂቃ የጠራ የግብ መፍጠር ሳይችል ቀርተው በ72ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን እድል ሳዲቅ ሼቾ ወደ ግብነት ለውጦት ልዩነቱን አስፋው ሲባል የግቡን አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች። አዲስ አበባዎች የፊት አጥቂ በመቀነስ የአማካዩን በቁጥር ቢያበዙም እምብዛም በጨዋታ ላይ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። በ80ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ የተከላካይ ስህተት ታክሎበት የተገኘውን ቅጣት ምት አቤል ብርሃኑ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመለወጥ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በሁለት ደቂቃዋች ልዩነት ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን ቅጣት ምት ካሌብ አበበ መትቶ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

በመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች በርካታ ያልተገቡ አጨዋወቶች የታዩ ሲሆን በተለይም በመጨረሻው ደቂቃ ጊት ጋትኮች ጥፋት ሰርቶብኛል ብሎ ካሌብ አበበ ወደ መሬት በወደቀበት ወቅት የድሬዳዋው ቢንያም አየለ ካላበት ስፍራ በፍጥነት በመምጣት እንዲሁም የአዲስ አበባው ፋሲል ጌታቸው ባደረጉት ግብግብ የሁለቱም የቡድን አባላቶች ወደ አላስፈላጊ እሰጣገባ ለመግባት ሲጋባዙ ታይቷል። ያም ሆኖ በቁጥር በዝተው የነበሩት ፀጥታ ኃይሎች ጉዳዩ ሳይባባሱ መቆጣጠር ችለዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዚሁ ምድብ በደረጃ ሰንጠረዥ ሶስተኛ እና አራተኛ የሁኑት ሀምበሪቾ እና ኢኮስኮን ያገናኘው ጨዋታ በእንግዳው ቡድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በሁለተኛው አጋማሽ ከኢትዮጵያ መድን ኢኮስኮን የተቀላቀለው ታምሩ ባልቻ ለኢኮስኮ የአሸናፊነቱን ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል።

ምድብ ሐ

ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ከምድቡ መሪ ሀድያ ሆሳዕና ያደረገው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ሆሳዕናዎች በኢቶል ሳሙኤል ነበር። ሆኖም ባለሜዳዋቹ በ47ኛው ደቂቃ ላይ በኩሴ መጨራ ግብ አቻ መሆን ችለዋል። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎም ሀዲያ ሆሳዕና ከተከታዩቹ ያለው የነጥብ ልዩነት ማስጠበቅ ሳይችል ቀርቷል።

አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ሺንሺቾን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል። የከፍተኛ ሊጉን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኘው ስንታየው መንግስቱ በ30ኛው ደቂቃ፣ ቴዲ ታደሰ ደግሞ በ60ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች አዞዎቹ መምራት የቻሉ ሲሆን በ71ኛው ደቂቃ ሺንሺቾዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ሚሊዮን ካሳ አስቆጥሯል።

ሚዛን አማን ላይ ቤንች ማጂ ቡና ከ ነቀምት ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ዘንድሮ በምድቡ ጥሩ ተፎካካሪ መሆን የቻሉት ነቀምት ከተማዎች ግብ ማስቆጠር የቻሉት ገና በ8ኛው ደቂቃ ላይ በዳንኤል ዳዊት አማካኝነት ነበር። ባላሜዳዋቹ ቤንች ማጂዎች የጨዋታው የመጨረሻው ደቂቃ ላይ በላይ አባይነህ ባስቆጠረው ጎል ነጥብ ተጋርተዋል።

ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከ ነገሌ ቦረና ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙት ቡታጅራዎች በ38ኛው ደቂቃ ላይ ሞፊድ እንድሪስ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል።

ቦንጋ ላይ የተደረገው የከፋ ቡና እና የሻሸመኔ ጫዋታ ተቋርጧል። የሁለቱ ጨዋታ እስከመጨረሻው ደቂቃ ምንም ግብ ሳይሰተናገድበት ቆይቶ መጨረሻ ላይ በተፈጠረ እሰጣ ገባ ሳይጠናቀቅ ቀርቶል።

የከፋ ቡድን ፕሬዝዳንት አቶ ሽፈራው ስለተፈጠረው ነገር እንዲ ብለዋል። “በጨዋታው ላይ የተፈጠረው ነገር የዳኛ ውሳኔን አለማክበር ነው። በጭማሪ ደቂቃ የከፋ ቡድን ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ የነበር ሲሆን የሻሸመኔ ቡድን ውሳኔውን በመቃወም አላስመታም ብሎ ቴክኒካል ክስም አስይዟል። እኔ እሰከማቀው ድረስ ክሱ ከተያዘ በኋላ የዳኛው ውሳኔ ፀድቆ በቀጣይ ክሱ የሚመለከተው አካል የሚስተላልፈው ውሳኔ መጠበቅ ነው። በአጭሩ የተከሰተው ይህ ነው።”

የሻሸመኔ ቡድን መሪ አቶ ካሊድ ትኩሌ በበኩላቸው ” የተፈጠረው ነገር በአጠቃላይ እንግዳ ነገር ነው። ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ መስመር ዳኛው የመልስ ምት ነው እያለ ባለበት ሰዓት ፍፁም ቅጣት ምት ነው በማለት የመሀል ዳኛው ውሳኔ አስተላልፏል። ከደጋፊ የነበረው ተፅእኖ ከፍተኛ ነበር። በውሳኔው ላይ ቴክኒካል ክስ አስመዝግበናል። በፍፁም አግባብ ያልሆነ እና አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት የተወሰነ ውሳኔ ነው።” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *