በሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና ወደ ሀገር ውስጥ በገባው አዲስ መሳርያ ዙርያ መግለጫ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ2020 በቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ይረዳው ዘንድ ለተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ላለፉት ቀናት መቀመጫውን ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አድርጎ ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት አስመልክቶ እንዲሁም በቅርቡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከካፍ በድጋፍ መልክ ስላገኙትና ለሙከራ በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሲሞከር ስለሰነበተው ካታ ፓልት በተሰኘው የጂ.ፒ.ኤስ መሣሪያ ዙርያ ያጠነጠነ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ረፋድ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተሰጥቷል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በመወከል ዋና አሰልጣኝዋ ሠላም ዘርዓይና የቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ ገለፃ ሰጥተዋል፡፡ በስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሠላም ዘርዓይ ምላሾች

ስለተጫዋቾቹ ምርጫ ተገቢነትን በተመለከተ

“በየትኛው የዓለም ክፍል የተጫዋቾች ምርጫ የሚደረገው በሁለት መልኩ ነው። አንደኛው አሰልጣኙ መጫወት ከሚፈልገው የጨዋታ መንገድ አንጻር ይሆኑኛል የሚላቸውን ተጫዋቾች ይመርጣል። ሌላው ደግሞ ተጫዋቾቹ በሊጉ ከሚጫወቱ ተጫዋች አንጻር በሚኖራቸው ወቅታዊ ብቃት የሚደረግ ምርጫ ነው፡፡ እኔ ወደ አሰልጣኝነት ቦታው የመጣሁት በጣም ዘግይቼ ነበር፤ በዚህም የቡድን ዝርዝር ለማሳወቅ በነበረኝ እጅግ ጠባብ ጊዜ ውስጥ ከዚህ በፊት በቅርበት በደንብ የማውቃቸውን እንዲሁም በወቅታዊ አቋም ረገድ የተሻሉ ብዬ ያመንኩባቸውን ተጫዋቾች ለማካተት ተሞክሯል፡፡”

ስላደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ

“ከዚህ ቀደም በነበረኝ የብሔራዊ ቡድን ቆይታ ከወንዶች ቡድኖች ጋር ጠንከር ያለ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገን ነበር። ነገርግን በዛን ወቅት በርከት ያሉ ጉዳቶች ተከስተው ነበር። ይህንን ከግምት በማስገባትና ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን ከመቀነስ እንዲሁም የቡድኑን የተነሳሽነት መጠን ከፍ ለማድረግ በማሰብ በሁለተኛ ዲቪዝዮን ከሚገኝ ቡድን ጋር ተጫውተን በሰፊ ጎል ማሸነፍ ችለናል፡፡”

ከዚህ ቀደም ከነበራት የብሔራዊ ቡድን ቆይታ አንጻር የአሁና ጫና ስለመኖሩ

“ባሳለፍነው ምርጫ የብሔራዊ ቡድኑን የማሰልጠን እድል ባገኘሁበት ወቅት እንደማንኛውም ወጣት አሰልጣኝ እድሉን በማግኘቴ በከፍተኛ ኩራትና ደስታ ቡድኑን ተረክቤ የተቻለኝን ጥሩ ስራ ለማከናወን ጥረት አድርጌያለሁ። በመጀመሪያው ቆይታዬ ጥሩ ልምድን ለማግኘት ችያለሁ። አሁን ደግሞ ከመጀመሪያው ቆይታዬ የተሻለ ነገር ለመስራት እጥራለሁ፡፡

የረቡዕ ተጋጣሚያቸው በሆነው ዩጋንዳ በቅርቡ በሴካፋ ውድድር ሁለት ግቦችን ከቆሙ ኳሶች ስለማስተናገዳቸውና ለመቅረፍ ስለተሰሩ ስራዎች

“በሴካፋ ውድድር ላይ በዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን 2-1ተሸንፈናል። እንደተባለው በተሸነፍንበት በዚያ ጨዋታ ላይ ያስተናገድናቸው ሁለቱም ግቦች የተነሱት ከቆሙ ኳሶች ነበር፤ ነገርግን በዚያው የሴካፋ ውድድር ላይ በነበሩት ቀሪ ጨዋታዎች ምንም አይነት የቆሙ ኳሶች አላስተናገድንም፡፡ ይሁንና የቆሙ ኳሶችን መከላከል እንደ ኢትዮጵያ በወንዶች በሴቶችም ሰፊ ችግር ነው። ይህንን ለመቅረፍ ዛሬና ነገ በሚኖሩን ልምምዶችም ጭምር ጠንክረን እየሰራንበት እንገኛለን፡፡”

ስለ ሎዛ አበራ ወቅታዊ አቋምና በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ግብ ያለማስቆጠር

“ሎዛ አበራ በሀገራችን ውስጥ ከሚገኙ አጥቂዎች በግምባር ቀደምነት የምትቀመጥ ናት ፤ እንደ አጥቂ በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ግብ አለማስቆጠሯ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው፡፡ ሴናፍ ዋቁማን፣ ሠርካዲስ ጉታን የመሠሉ አጥቂዎች ደግሞ አብረዋት መኖራቸው ጫናን ከመጋራት በዘለለ በይበልጥ በጨዋታ እንቅስቃሴ ይረዷታል ብዬ አስባለሁ፡፡”


የቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ ምላሾች

ስለቡድኑ ዝግጅትና መንፈስ

“በሀገራችን ቡድኖች ከዚህ ቀደም ያለውን ደካማ የታክቲክ አረዳድ ለመቅረፍ ይረዳን ዘንድ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱም ረገድ የተሻለ ሆነን ለመቅረብ ከአሰልጣኛችን ጋር በመሆን ጠንካራ ስራዎች እየሰራን እንገኛለን። የቡድኑ መንፈስ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፤ እንዴት ይህን ጨዋታ አሸንፈን ማለፍ እንደምንችል በሜዳ ላይ ከምንሰራው ልምምድ በተጨማሪ በጋራ ሆነን እየሰራን እንገኛለን፡፡”

ከወቅታዊ አቋሟ ጋር ስለሚነሱ ጉዳዮች

” ስዊድን በነበረኝ ቆይታ በተጫወትኩባቸው ጨዋታዎች ላይ ግቦችን አስቆጥሪያለሁ ፤ የመረጃ እጦት ሊሆን ይችላል እንጂ በርካታ ግቦችን አስቆጥሪያለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩም ወዲህ በተመሳሳይ በሶስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን አስቆጥሬያለሁ፡፡ ከግለሰብ ቡድን ይበልጣል፤ እኔ በወዳጅነት ጨዋታ ግብ ባላስቆጥርም ጥሩ ብቃት ያላቸው አጥቂዎች አሉ እነሱም ማስቆጠር ችለዋል፡፡ አጥቂ እንደመሆኔ ሀገሬ ከእኔ በጣም ብዙ ነገር ትጠብቃለች ፤ እንደአጠቃላይ ግን ማለት የምችለው አሁንም ብቃቴ አልወረደም በረቡዕ ጨዋታም ግብ አስቆጥራለሁ፡፡”

በመቀጠልም ከካፍ በእርዳታ ስለተገኘውና በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ልምምድ ላይ በሙከራነት ሲተገበር ስለነበረው ዘመናዊው ካታ ፓልት ጂ.ፔ.ኤስ መሣሪያ የስፓርት ሳይንስ ባለሙያ በሆኑት ዶ/ር ዘሩ በቀለ ስለመሳሪያው ገለፃ ተሰጥቷል፡፡

ካፍ ለእያንዳንዱ አባል ሀገራት እነዚሁን እያንዳንዳቸው 60 ግራም የሚመዝኑ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የጂ.ፒ.ኤስ መሣሪያዎች በመጀመሪያ ዙር 75 መሣሪያዎችን ለመስጠት በገባው ቃል መሠረት 50 የሚሆኑት ኢትዮጵያ መድረሳቸውን የጠቀሙት ባለሙያው መሣሪያው የሰውነት ብቁነትን ከመለካት በዘለለ ታክቲካዊ ትንተናዎች የሚረዱ ግብዓቶችን የሚሰጥ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

መሣሪያው አንድ ተጫዋች የሚሸፍነውን ርቀት፣ ያስመዘገበውን ፍጥነት፣ ጉልበትና መሠል መረጃዎችን የሚመዘግብ ይሆናል። በጥቅሉ 1000 የሚጠጉ መረጃዎችን በአንድ ሰከንድ ውስጥ የመመዝገብ አቅም አለውም ተብሏል፡፡

ከመሣሪያው የሚሰበሰቡት ግብዓቶች በቀጣይ የሚኖሩ የልምምድ መርሃ ግብሮችን ለመቅረፅ እንዲሁም የተጫዋቾችን ጤንነት በመጠበቅ ከጉዳት ለመከላከልም ሊውል ይችላል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ዘሩ አይይዘውም መሣሪያው አሁን ለሙከራ ያክል ተጫዋቾች ያልለመዱት ስላልሆነ በልምምድ ላይ አድርገውት እንዲሰሩ በማድረግ ብቻ የተገደበ እንደሆነና በቀጣይ በፉክክር ጨዋታዎች ላይ ይውላልም ብለዋል፡፡

ሌላው ዶክተሩ ያነሱት ሀሳብ መሳሪያውን መጠቀም ከጀመሩ አንስቶ መሻሻሎች እንዳሉ ገልፀው በዚህም በአካል ብቃት መለኪያዎች አንጻር ከዓለምአቀፍ መመዘኛ መስፈሮቶች ጋር ተቀራራቢ ውጤቶች መመዝገባቸውን፤ በተቃራኒው ከጉልበትና የአንድ ለአንድ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ልኬቶች ግን ከባድ የቤት ስራ እንደሚጠብቀን የሚጠቁሙ ናቸው ብለዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *