ሙሉጌታ ዓምዶም ደደቢትን ተቀላቅሏል

በጥር የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች ያስፈረሙት ደደቢቶች አሁን ደሞ የስሑል ሽረው አምበል ሙሉጌታ ዓምዶም የግላቸው አድርገዋል።

በ2008 መጨረሻ መቐለን በመልቀቅ ስሑል ሽረን የተቀላቀለውና በቡድኑ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታ ያደረገው ሙሉጌታ በአጥቂ ፣ ተከላካይ እና የመስመር አማካይ መጫወት የሚችል ሲሆን ከአሸናፊ እንዳለ ቀጥሎ የቀድሞ አሰልጣኙን ተከትሎ ወደ ሰማያዊዎቹ የመጣ ሁለተኛ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ያለፉት ሁለት ዓመታት ተከላካይ ሆኖ ከመጫወቱ በፊት በመቐለ ቆይታው ለበርካታ ዓመታት የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ይህ ተጫዋች በዳንኤል ፀሐዬ አጨዋወት ውስጥ ቁልፍ ቦታ የሆነውን የመስመር አማካይነት ሚና ተሰጥቶት ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሰማያዊዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት መጀመርያ ከኢኳቶርያል ጊኒያዊው የመስመር አማካይ ሮበን ኦባማ መለያየታቸው ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡