የባየርን ሙኒክ አመራሮች አዲስ አበባ ይመጣሉ

የጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየርን ሙኒክ የክብር አምባሳደር እና አመራሮች ከፊታችን እሁድ ጀምሮ አዲስ አበባ ይገባሉ።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽና እና የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጋራ በመሆን ባመቻቹት ዕድል መሰረት የባየርን ሙኒክ የክብር አምባሳደር የሆነው ብራዚሊዊው የቀድሞ የክለቡ አጥቂ ጂኦቫኒ ኤልበር፣ የክለቡ ዋና ስራ አስፈፃሚ ካርል ሄይንዝ ሩሚኒገ እና ሌሎችም ግለሰቦች ጨምሮ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ይሆናል።

ለቀናት በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ ተግባራት ያከናውናሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በዋናነት በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር በሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ተሳታፊ ከሆኑት ክለቦች መካከል ኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሠላም፣ ኢ/ወ/ስ አካዳሚ እና ኢትዮ ኤሌትሪክ ጨምሮ የሰውነት ቢሻው አካዳሚ ቡድኖች እያንዳንዳቸው አስር አስር ተጫዋቾችን በመላክ የፊታችን ረቡዕ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚደረጉ ጨዋታዎች በኢትዮጵያ እግርኳስ ታዳጊዎች ላይ እየተሰራ ያለውን እንቅስቃሴ ከመገምገማቸው ባሻገር ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉትን ተጫዋቾች የተሻለ እድል የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻቻሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪ የባየርሙኒክ የረጅም ዓመት ስፖንሰር የሆነው ታዋቂው የስፖርት ትጥቆች አምራች አዲዳስ በኢትዮጵያ ሊከፍተው ያሰበው እና በግንባታ ላይ የሚገኘውን የሽያጭ ማዕከል ከመጎብኘታቸው ባሻገር ኦሎምፒያ የሚገኘው የአዲዳስ ይፋዊ የምርት አከፋፋይ የሆነውን ድርጅት ማክሰኞ የሚዲያ አከላት በተገኙበት ጉብኝት ያደርጋሉ። ከጋዜጠኞች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉም ተብሏል።

የአምስት ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮኖቹ አዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር በቀጣይ በሚኖረው ሁለተናዊ ግኑኝነት ዙርያ ውይይት ያደርጋሉ፤ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉም ተብሎ ይጠበቃል።

የክለቡ ስራ አስፈፃሚ በመሆን እየሰሩ የሚገኙት ካርል ሄይንዝ ሩሚኒገ የቀድሞ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን እና ባየርን አጥቂ የነበሩ ሲሆን በ1980 እና 81 የባሎን ደ’ ኦር አሸናፊ ናቸው። ብራዚላዊው ጂኦቫኒ ኤልበር ደግሞ ከ1997 እስከ 2003 ለክለቡ የተጫወተ ስመጥር አጥቂ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡