ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ መከላከያ

የ20ኛው ሳምንት የመጀመሪያ የሆነውን የወልዋሎ እና መከላከያ ጨዋታ እንደሚከተለው እናስዳስሳችኋለን።

በትግራይ ስታድየም ነገ 09፡00 ላይ ወልዋሎ ዓ /ዩ መከላከያን የሚያስተናግድበት የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ ይከናወናል። ሁለተኛውን ዙር በድል የጀመሩት ወልዋሎዎች በተከታታይ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማሳካት ቢሳናቸውም ሳምንት ወደ ሀዋሳ ተጉዘው በፕሪንስ ሰቨሪንሆ ብቸኛ ግብ ደቡብ ፖሉስን በገጠሙበት ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል። በውጤቱም የነጥብ ስብስባቸውን 27 በማድረስ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ መቀመጥ ችለዋል። የሌሎችን ነጥብ ጠብቀው እስከ አምስተኛነት ከፍ የማለት ዕድል ያላቸው ቢጫ ለባሾቹ በነገው ጨዋታ ለመልሶ ማጥቃት ምቹ በሆኑት የመስመር ተሰላፊዎቻቸው ደካማውን የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል እንደሚፈትኑ ይጠበቃል። ወልዋሎዎች በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ተሳታፊ የነበረው ብርሃኑ አሻሞን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት የማያሳልፉ ሲሆን ሌላኛው አማካይ አፈወርቅ ኃይሉም ላለፉት ሁለት ቀናት ልምምድ ቢሰራም ለጨዋታው ብቁ ባለመሆኑ አይሰለፍም። በመሆኑም ቡድኑ መሀል ክፍሉ ላይ የሚያደርጋቸው አስገዳጅ ቅያሪዎች በመጀመሪያዎቹ ተመረጮቹ መጠን መግባባትን የሚያመጣ እና በቦታው ሊኖር የሚችለውን የመከላከያ ተሰላፊዎች እንቅስቃሴ የሚገታ መሆን ይጠበቅበታል።

ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ከገጠሟቸው በኋላ ድሬዳዋ ላይ ነጥብ ተጋርተው የተመለሱት መከላከያዎች ባሳላፍነው ሳምንት በደደቢት ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናግደዋል። የቡድኑ የመከላከል ስህተቶች ዳግም ገዝፈው በታዩበት ጨዋታ ዳዊት እስጢፋኖስን ሳይጠቀም ባልተለመደ ሁኔታ የቀረበው አማካይ ክፍሉም ተፅዕኖው ወርዶ ታይቷል። ከዚህ ውጪ ከተደጋጋሙ ሽንፈቶች የመነጨ በሚመስል መልኩ የተፈጠሩት መልካም የሚባሉ የግብ ዕድሎችም ሲመክኑ ታይቷል። በተደጋጋሚ እነዚህን ደካማ ጎኖቹን ማስተካከል ያልቻለው መከላከያ የነገው ጨዋታ ውጤት ይበልጥ የሚያስፈልገው በመሆኑ ለመጥቃት እንደሚደፍር ቢጠበቀም መሰል ድክመቶቹ ግን ከኋላ የሚተወውን ክፍተት ዳግም የስጋቶቹ ምንጭ ሊያደርገው ይችላል። አበበ ጥላሁንን በቀይ ካርድ ቅጣት የማያሰልፈው የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን ከምንይሉ ወንድሙ በቀር በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን ከመቐለ በሽንፈት ከተመለሰ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ራሱን ሊያገኝ ይችላል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ዓ.ዩ አምና ሊጉን ከተቀላቀለ አንስቶ ቡድኖቹ ከተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱ በመከላከያ የ2-1 1-0 አሸናፊነት የተጠናቀቁ ነበሩ። ዘንድሮ ደግሞ ወልዋሎ የ1-0 ድል ቀንቶታል።

– ከሜዳው ውጪ ስምንት ጨዋታዎችን ያከናወነው መከላከያ ሁለቱን ብቻ በድል ሲወጣ በሦስቱ ነጥብ ተጋርቶ ሦስት ሽንፈቶች ገጥመውታል።

– ትግራይ ስታድየም ላይ አስር ጨዋታዎችን ያደረገው ወልዋሎ ሦስቴ ድል ሲቀናው ሁለት ሽንፈት እና አራት የአቻ ውጤቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በመራቸው አምስት ጨዋታዎች 14 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ /ዩ (4-2-3-1)

አብዱላዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – በረከት ተሰማ – ደስታ ደሙ – ብርሀኑ ቦጋለ

ኤፍሬም ኃይለማርያም – አማኑኤል ጎበና

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – አብዱርሀማን ፉሴይኒ – ኤፍሬም አሻሞ

ክርስቶፈር ቺዞባ

መከላከያ (4-2-3-1)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አዲሱ ተስፋዬ – ዓለምነህ ግርማ

ቴዎድሮስ ታፈሰ – በኃይሉ ግርማ

ዳዊት ማሞ – ዳዊት እስጢፋኖስ –ፍሬው ሰለሞን

ፍፁም ገብረማርያም


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡