ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ባህርዳር ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉት ተጠባቂ ጨዋታዎች ውስጥ ዋነኛው የሆነውን የባህር ዳር ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ተከታዩ የዳሰሳችን ትኩረት ይሆናል።

በሁለተኛው ዙር ከሁለቱ የዋንጫ ተፎካካሪዎች ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ ሦስት ነጥብ ወስደው ደረጃቸው ያሻሻሉት የጣና ሞገዶች በነገው ዕለት ከሊጉ መሪ ጋር በሚያደርጉት ፍልምያ ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆኑ ለመረዳት ያለፉትን ሁለት የሜዳቸው ጨዋታ ማየት ቀላል ነው። በሜዳቸው ጥሩ የማሸነፍ ክብረ ወሰን ያላቸው የጣና ሞገዶቹ እንዳለፉት ጨዋታዎች በነገው ጨዋታም በሁለቱም የመስመር አጥቂዎቻቸው ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ሲጠበቅ ለወትሮው ወደ መሀል ሜዳ የቀረበ የቦታ አያያዝ ያለው የተከላካይ ክፍላቸው በነገው ጨዋታ ለሁለቱ የመቐለ ፈጣን አጥቂዎች ኢላማ አድርገው በረጅሙ የሚላኩትን ኳሶች በቀላሉ ለማምከን ወደ ራሱ ሳጥን ተጠግቶ ይከላከላል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ዓመት ወራጅ ቀጣና ካሉት ቡድኖች (ደደቢት እና ስሑል ሽረ) ከተደረጉት ጨዋታዎች ውጪ ከአንድ በላይ ግብ ማምረት የተሳናቸው የጣና ሞገዶቹ በነገው ጨዋታ ከመቐለ ተከላካዮች የሚጠብቃቸው ፈተና እና በዚህ ዓመት ከታዩት ጠንካራ የተከላካይ ጥምረቶች መሃል አንዱ የሆነው የባህርዳር ከተማ የተከላካይ ጥምረት ከፈጣኖቹ የመቐለ አጥዎች የሚጠብቀውን ተመሳሳይ ፈተና እንዴት ይወጣዋል የሚሉት ጉዳዮች በነገው ጨዋታ የሚጠበቁ ነጥቦች ናቸው። ባህር ዳሮች ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በጉዳት ወንደሜነህ ደረጄን ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ አያገኙም።

ከተከታታይ አስር ጨዋታዎች ማሸነፍ በኃላ መንገራገጭ አሳይተው የነበሩት ሰብዓ እንደርታዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻን አሸንፈው ከተከታዮቻቸው ያላቸውን ልዩነት ከፍ አድርገው ለዚህ ጨዋታ እንደመቅረባቸው ከባለፉት ሳምንታት ውጤት መጥፋት በኃላ በተሻለ የማሸነፍ ስነ-ልቦና ተላብሰው ትልቁን ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ባለፉት ጨዋታዎች በመስመር በሚደረጉ ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች እና ከተከላካዮች ጀርባ ላይ ያነጣጠሩ ረጃጅም ኳሶች ለመጠቀም ሲሞክሩ የታዩት ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታም በተመሳሳይ መንገድ ለማጥቃት ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይታሰባል።

በሚከተሉት ጠባብ የ4-4-2 አሰላለፍ ወሳኝ ሚና ያላቸውን በሁለቱ መስመር የሚሰለፉት የመስመር ተከላካዮች ጉዳት እንደሚፈለገው ለአጨዋወቱ የሚሆን ሁነኛ ተተኪ ያላገኙት መቐለዎች በነገው ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ውጤታማ ወዳደረጋቸው 3-5-2 የሚመለሱበት ዕድል የሰፋ እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ፈጣኑን የባህርዳር የመስመር አጨዋወት ለመመከት አጨዋወቱን የሚመርጥበት ሌላ ምክንያት ነው። መቐለዎች በተመሳሳይ በቀኝ መስመር ተከላካይ የሚሰለፉትን አቼምፖንግ አሞስ እና ስዩም ተስፋዬን በጉዳት አያገኙም የባለፈው ሳምንት ጨዋታ በቅጣት ያለፈው ጋናዊው አጥቂ ኦሴይ ማውሊ ከቅጣት መልስ ቡድኑን ያገለግላል።

የእርሰ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በአምስተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር የተገናኙበት የመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታቸው በመቐለ 70 እንደርታ 1-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

– አሁንም በሜዳቸው በመጠንካራ አቋማቸው የቀጠሉት የጣና ሞገደቹ ምንም ሽንፈት ያልገጠማቸው ሲሆን አምስት የድል እና አራት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።

– መቐለ 70 እንደርታ ሰባት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ሲያከናውን በመጀመሪያ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ቢያገኘውም ቀጥሎ አቻ በመውጣት ከዚያም ሦስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቧል ፤ በመጨረሻው ጨዋታው ደግሞ በፋሲል ተሸንፏል።

ዳኛ

– ጨዋታው በተጋጣሚዎቹ መካከል ከሚያስተናግደው ትተጠባቂ ፉክክር ባለፈም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ከአምስት ዓመታት በላይ ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ የምትመለስበትም ጭምር ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሐሪሰን ሄሱ

ማራኪ ወርቁ – አሌክስ አሙዙ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ – ደረጄ መንግስቱ – ኤልያስ አህመድ

ዜናው ፈረደ – ፍቃዱ ወርቁ – ግርማ ዲሳሳ

መቐለ 70 እንደርታ (3-5-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ቢያድግልኝ ኤልያስ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ

ያሬድ ሐሰን – ሐይደር ሸረፋ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ያሬድ ከበደ – አማኑኤል ገብረሚካኤል


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡