ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ

ከነገው የሊጉ መርሐ ግብር ውስጥ ዘግየት ብሎ የሚጀምረው የቡና እና ባህር ዳር ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል። 

ዛሬ 10፡00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም ይከናወናል። ሁለተኛውን ዙር በሽንፈት የጀመሩት ቡናዎች በወልዋሎ እና ደደቢት ድል መነቃቃት አሳይተው የነበረ ቢሆንም በቀጣዮቹ የፋሲል እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ደግሞ አንድ ነጥብ ብቻ ነበር ያሳኩት። ወጥነት የጎደለው አካሄዳቸውም ከዋንጫ ፉክክሩ በእጅጉ ያራቃቸው ሲሆን የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍም ነጥባቸውን ከ30  በላይ ከፍ ወደማድረግ እና ወደ 6ኛ ደረጃ የመሸጋገር ፋይዳ ብቻ ነው የሚኖረው። ከቡና በሦስት ነጥብ ከፍ ብሎ የተቀመጠው ባህር ዳርም ከጨዋታው በሚገኙ ነጥቦች ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የመጠጋት ዓላማ ይኑረው እንጂ ሙሉ ለሙሉ በፉክክሩ ውስጥ እየተሳተፈ ነው ለማለት ይከብዳል። በርግጥ የጣና ሞገዶቹ ሳምንት የሊጉን መሪዎች መርታታቸው ከፋሲል እና ሲዳማ አለማሸነፍ ጋር ተዳምሮ ቡድኖቹን እግር በእርግር ለመከተል ያስቻላቸው ሲሆን ይበልጥ ለመጠጋትም ከዛሬው ጀምሮ ቀጣይ ጨዋታዎቻቸውን በትኩረት ማድረግም ይጠበቅባቸዋል። 

ኢትዮጵያ ቡና ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ባህር ዳሮች ደግሞ በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ በማሰብ እንደሚፋሉ በሚጠበቁበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በዋነኝነት ከመስመር አጥቂዎቻቸው በሚነሱ ኳሶች ላይ የሚመረኮዙ ይመስላል። ይህም ጨዋታው በሁለቱ ኮሪደሮች በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ፣ ተሻጋሪ ኳሶች እና በመስመር እና በመሀል ተከላካዮች መካከል በሚኖሩ ክፍተቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ብቃት ሊወሰን እንደሚችል ይጠቁማል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል የአልሀሰን ካሉሻ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መምጣት የተጨዋቹን በራስ መተማመን ከፍ ከማድረግ ጋር ተያይዞ አማካይ ክፍል ላይ ለሚታይበት ድንገተኛ መረበሽ መሻሻልን ሊያመጣለት እንደሚችል ሲታሰብ መልካም አቋም ላይ የሚገኘው የሁሴን ሻቫኒ የግራ መስመር እንቅስቃሴም የቡድኑ የጥቃት ሂደት ዋነኛ መንገድ እንደሚሆን ይታሰባል። በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ተመስገን ካስትሮ ፣ ሚኪያስ መኮንን ፣ ኢስማ ዋቴንጋ ፣ ሱለይማን ሎክዋ እና ክሪዚስቶም ንታንቢ አሁንም አይደርሱለትም። በአንፃሩ ከአምበሉ ፍቅረሚካኤል አለሙ ጉዳት ውጪ ሙሉ ስብስባቸው ለጨዋታው ዝግጁ የሆነላቸው ባህር ዳሮች ከአማካይ ክፍላቸውም ሆነ ከኋላ ለፈጣኖቹ የመስመር አጥቂዎቻቸው በሚያደርሷቸው ኳሶች ላይ ዕምነታቸውን የሚጥሉ ይመስላል። በተለይም ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ወሰኑ ዓሊ የቡናን የማጥቃት ሂደት ተከትሎ በሚያገኘው ክፍተት የቡድኑን የጨዋታ ዕቅድ ለመተግበር ምቹ ሲያደርገው ግብ በማስቆጠሩ እየቀናው ያለው የመስመር ተከላከያቸው ሣለአምላክ ተገኝም በቀድሞ ክለቡ ላይ ሰሞንኛ አቋሙን መድገም ከቻለ ለጣና ሞገዶቹ ተጨማሪ ጉልበት ይሆናቸዋል። 

የእርስ በርስ ግንኘነት እና እውነታዎች

– ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተገናኘበትን የመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታ በጃኮ አራፋት ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል።

– ዘንድሮ በአዲስ አበባ ስታድየም 12 ጨዋታዎችን ያከናወኑት ኢትዮጵያ ቡናዎች አምስቱን በድል ሲወጡ አራት የአቻ እና ሦስት የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበዋል።

– ባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው አስር ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአራቱ ነጥብ ተጋርቶ በአራቱ ደግሞ ተሸንፎ ተመልሷል።
                                                     

ዳኛ

– ስምንት  ጨዋታዎችን ዳኝቶ 37 የቢጫ ካርዶችን እንዲሁም ሁለት ቀጥታ ቀይ ካርዶችን የመዘዘው እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው  አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ወንድወሰን አሸናፊ

አህመድ ረሺድ – ቶማስ ስምረቱ  – ወንድይፍራው ጌታሁን – እያሱ ታምሩ

          
አማኑኤል ዮሀንስ – ሄኖክ ካሳሁን – ካሉሻ አልሀሰን

አስራት ቱንጆ – አቡበከር ናስር – ሁሴን ሻቫኒ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሐሪሰን ሄሱ

ሣለአምላክ ተገኝ – አሌክስ አሙዙ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ – ደረጄ መንግስቱ – ኤልያስ አህመድ

ዜናው ፈረደ – ፍቃዱ ወርቁ – ወሰኑ ዓሊ