የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ40 ቀናት መቋረጥ በኋላ ነገ እና ከነገ በስቲያ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡ 5 ሳምንት በተከታታይ ከተካሄደ በኋላ በድጋሚ ለ44 ቀናት የሚቋረጠው ሊጋችን ዙርያ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አመዛኞቹ የክለብ አሰልጣኞች የውድድሩ ለረጅም ጊዜ መቋረጥ ችግር እንደፈጠረባቸው ሲናገሩ አንዳንዶቹ ቡድናቸውን ለማሻሻል ጊዜ ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡
የአሰልጣኞቹን አስተያየት እንደሚከተለው አጠር አጠር አድርገን አቅርበነዋል:-
አሸናፊ በቀለ (አዳማ ከነማ)
‹‹ ለአርባ ቀናት ከውድድር ርቆ መመለስ ቤት አፍርሶ ድጋሚ የመገንባት ያህል ከባድ ነው፡፡ ››
ታረቀኝ አሰፋ (ዳሽን ቢራ)
‹‹ ውድድሩ በመቋረጡ እንደ ክለብ ደስተኛ አይደለንም፡፡ ውድድሩ በመቋረጡ 20 ቀን እረፍት ሰጥተን 20 ቀን ልምምድ ለመስራት ተገደናል፡፡ እንደ ሲቲ ካፕ አይነት ውድድር በማዘጋጀት ተጫዋቾቹ ውድድር ላይ እንዲቆዩ አስበን ነበር፡፡ ነገር ግን ከፋይናንስ አንጻር አስቸጋሪ ነው፡፡
የ2013 ቻን ያስተናገደችው ደቡብ አፍሪካ በውድድሩ ወቅት ሊጓ አልተቋረጠም ነበር፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ልምድ በመውሰድ ሊጉ የማይቋረጥበት መንገድ ቢፈለግ ጥሩ ነው፡፡››
ጌታቸው ዳዊት (ደደቢት)
‹‹ ቡድናችን በጥሩ ሁኔታ የውድድር ዘመኑን በጀመረበት ሁኔታ በመቋረጡ ደስተኛ አልነበርንም፡፡ መቋረጡ ጠቅሞናል ልንል የምንችለው በጉዳት ያጣናቸው ተጫዋቾችን መልሰን እንድናገኝ ማድረጉ ነው፡፡ ››
መሳይ ተፈሪ (ወላይታ ድቻ)
‹‹ በእርግጥ መቋረጡ ለሊጉ ጥሩ አይደለም፡፡ ለኛ ግን ጠቅሞናል፡፡ በሀዋሳ ሲቲ ካፕ እና የመጀመርያዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ቡድኔ አልተደራጀም ነበር፡፡ መቋረጡ የቡድን ስራ በሚገባ እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ ››
ውበቱ አባተ (ሀዋሳ ከነማ)
‹‹ ለተጫዋቾቻችን የረጅም ጊዜ እረፍት ብንሰጥ ሲመለሱ ብቃታቸው ወርዶ ነው የሚመለሱት፡፡ ካለ ውድድር ልምምድ ብቻ ብንሰራ ደግሞ መሰላቸት ይመጣል፡፡ በዚህ በኩል ተቸግረን ነበር፡፡
‹‹ በሊጉ አሉ የሚባሉ ተጫዋቾችን ይዘን ሊጉን በማቋረጥ ውድድሮች አድርገን ውጤት ካላመጣን ወጣቶች ላይ አንዳንድ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን አካተን ብንወዳደር ሊጉም ሳይቋረጥ ወጣት ተጫዋቾችም ለብሄራዊ ቡድን የመጫወት ልምድ ያገኛሉ፡፡
‹‹ በሴካፋ ውድደር ላይ ከአንድ ክለብ በርካታ ተጫዋች ቢመረጥም በቋሚ 11 ውስጥ ከአንድ ክለብ የምንመለከታቸው ተጫዋቾች ቁጥር ከ2 አይበልጥም፡፡ ከአንድ ክለብ በብዛት ተመርጠው ተጠባባቂ ከሚሆኑ እንደከዚህ ቀደሙ ከየክለቡ አመጣጥነን በመጥራት ሊጉ ሳይቋረጥ ውድድሩን ማካሄድ እንችል ነበር፡፡ ››
ገብረመድህን ኃይሌ (መከላከያ)
‹‹ በውድድሩ መቋረጥ ተቸግረናል፡፡ ውድድሮች በአግባቡ ሳይጀመሩ እንደ አዲስ እረፍት መስጠት እና በልምምድ ማሳለፍ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቡድኔን እንደምፈልገው ለመገንባት አዳጋች አድርጎብኛል፡፡››
ግርማ ታደሰ (ሀድያ ሆሳእና)
‹‹ ከብሄራዊ ሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ለፕሪሚየር ሊጉ ለመዘጋጀት የነበረን ጊዜ አጭር በመሆኑ መቋረጡ ጠቅሞናል፡፡ የወዳጅነት ጨወታዎች በማድረግ ቡድኔን ለማሻሻል ረድቶኛል፡፡ ››
ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)
‹‹ በሲቲ ካፑ እና ፕሪሚየር ሊጉ የመጀመርያ ጨዋታዎች ላይ የተደራጀ ቡድን ይዘን አልቀረብንም ነበር፡፡ በተቋረጠባቸው 40 ቀናት የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ አዲሶቹን ተጫዋቾች ከነባሮቹ ጋር ለማዋሃድ ጊዜ አግኝተናል፡፡ ››