ሽመልስ የሚጫወትበት ፔትሮጀት ሲሸነፍ ፍቅሩ ተፈራ በህንድ እየተሳካለት አይደለም

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ዕሁድ በተደረገ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያዊው የአጥቂ አማካይ ሽመልስ በቀለ ፔትሮጀት በአረብ ኮንትራክተርስ 2-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ለ81 ደቂቃዎች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ የአረብ ኮንትራክተርስን የድል ግቦች መሃመድ ሳሚር 31ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ጣሂር መሃመድ ጣሂር በ89ኛው ደቂቃ አስመዝግበዋል፡፡ የስዌዙ ክለብ ሽንፈቱን ተከትሎ በ5 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡

ፔትሮጀት አሰልጣኝ የሆነው የቀድሞ የፈርኦኖቹ ኮከብ አህመድ ሃሰን ከክለቡ የመባረር ዕድሉ እየሰፋ መምጣቱን ከግብፅ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አህመድ ሃሰን ክለቡን ለማሰልጠን የተስማማው ባሳለፍነው ክረምት ነበር፡፡

የሌላው ኢትዮጵያዊ አጥቂ ዑመድ ኡኩሪ ክለብ የሆነው ኢኤንፒፒአይ አስዋንን 3-2 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 8ኛ አሳድጓል፡፡ በጨዋታው ላይ ዑመድ አልተሰለፈም፡፡

በህንድ ሂሮ ሊግ ለቼኔይን እየተጫወተ የሚገኘው ፍቅሩ ተፈራ አምና በአትሌቲኮ ካ ልኮታ እንዳሳለፈው በቼኔይን የተሳካ ግዜን እያሳለፈ አይደለም፡፡ በውድድር ዘመኑ ምንም ግብ ያላስቆጠረው ፍቅሩ የተጠባባቂ ወንበር ማሞቁን ተያይዞታል፡፡

ፍቅሩ ቋሚ ሆኖ በተሰለፋባቸው 4 ጨዋታዎች በጣሊያናዊው ማርኮ ማታሬዚ የሚሰለጥነው ቼኔይን ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡ ፍቅሩ የፊት መስመሩን ለኮሎምቢያው ጆን ስቲቨን ሜንዶዛ ማስረከብ ተገዷል፡፡ ከብራዚሉ ክለብ ኮረንቲያስ በውሰት የመጣው ሜንዶዛ በውድድር ዘመኑ 11 ግቦችን አስቆጥሮ የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን ፍቅሩ ግብ ባያስቆጥርም አሰልጣኙ ማታሬዚ ፍቅሩ ጠንክሮ ልምምድን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ወደ መጠናቀቂው የቀረበው የህንድ ሂሮ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ታውቀዋል፡፡ የፍቅሩው ቼኔይን ፑኔ ሲቲን 1-0 በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡ ፍቅሩ ባልተሰለፈበት ጨዋታ ለቼኔይን የማሸነፊያ ግብ ጄጄ ላልፕካሉሃ በ64ተኛ ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡ ቼኔይን ሊጉን በ22 ነጥብ 3ተኛ ሆኖ ሲጨርስ በቀድሞ የብራዚል ኮከብ ዚኮ የሚሰለጥነው ኤፍሲ ጎአ የሊጉ አናት ላይ በመቀመጥ አጠናቅቋል፡፡

ዴሊህ ዳይናሞስ እና አትሌቲኮ ደ ኮልካታ ሌሎች ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀሉ ክለቦች ናቸው፡፡ የህንድ ሂሮ ሊግ በ8 ቡድኖች መካከል ሲካሄድ ከ1-4 የሚወጡ ቡድኖች ወደ ግማሽ ፍፃሜው በቀጥታ በማለፍ የሊጉን ክብር ለማግኘት ይፋለማሉ፡፡ በዚህም መሰረት ቼኔይን ከ አትሌቲኮ ደ ኮልካታ እንዲሁም ዴሊህ ዳይናሞስ ከ ኤፍሲ ጎአ በግማሽ ፍፃሜው የሚገናኙ ይሆናሉ፡፡ ፍቅሩ ተፈራ ዓምና በታሪክ የመጀመሪያውን የህንድ ሂሮ ሊግን ግብ አስቆጥሯል እንዲሁም የሊጉን ዋንጫ ከአትሌቲኮ ደ ኮልካታ ጋር ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *