ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ ለአለም ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅት ይጀምራል

– ወደ አለም ዋንጫ ለማለፍ ሁለት ጨዋታ ብቻ ከፊቱ ይጠብቀዋል

 

የ2016 የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች የአለም ዋንጫ ከሴፕቴምበር 30-ኦክቶበር 21 (ከመስከረም 2009 አጋማሽ እስከ ጥቅምት መጀመርያ) ድረስ በጆርዳን አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያም በታርኳ ለመጀመርያ ጊዜ በማጣርያ ውድድሩ ላይ ዘንድሮ ትካፈላለች፡፡

ከ17 አመት በታች ቡድኑ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ቡድንን ለአለም ዋንጫ ለማሳለፍ ከጫፍ ደርሰው በነበሩት አሰልጣኝ አስራት አባተ የሚመራ ሲሆን አሰልጣኙም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር እና ከኢትዮጵያ ታዳጊዎች አካዳሚ ታዳጊዎን በመመልመል ላይ ይገኛሉ፡፡

አሰልጣኝ አስራት ምልመላቸውን እንደጨረሱ በሳምንቱ መጨረሻ ዝግጅት እንደሚጀምሩ የሚጠበቅ ሲሆን ኢትዮጵያ የመጀመረያ ጨዋታዋን ከታህሳስ 29 እስከ ጥር 1 ባሉት ቀናት ውስጥ ከካሜሩን ጋር ታደርጋለች፡፡

ኢትዮጵያ በማጣርያው በቀጥታ የመጀመርያ ዙር ውስጥ ከተካተቱትና ቅድመ ማጣርያ ከማያደርጉት 9 ሃገራት መካከል አንዷ መሆን ስትችል በማጣርያው በአጠቃላይ 15 ሃገራት ይሳተፋሉ፡፡ በማጣርያው እርስ በእርስ ተፋልመው የሚያልፉ 3 ሃገራትም አፍሪካን ወክለው በጆርዳኑ ከ17 አመት በታች ሴቶች አለም ዋንጫ ላይ ይሳተፋሉ፡፡

የኢትዮጵያ ጨዋታዎች

አንደኛ ዙር

ታህሳስ 29 ፣ 30 ወይም ጥር 1 – ካሜሩን ከ ኢትዮጵያ ( የመጀመርያ ጨዋታ በካሜሩን ሜዳ)

ጥር 13 ፣ 14 ወይም 15 – ኢትዮጵያ ከ ካሜሩን (የመልስ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሜዳ)

ወደ 2ኛ ዙር ካለፈች

መጋቢት 2 ፣ 3 ወይም 4 – የግብፅ እና ጅቡቲ/ዲሞክራቲክ ኮንጎ አሸናፊ ከ ኢትዮጵያ (የመጀመርያ ጨዋታ ከሜዳችን ውጪ)

መጋቢት 16 ፣ 17 ወይም 18 – ኢትዮጵያ ከ የግብፅ እና ጅቡቲ/ዲሞክራቲክ ኮንጎ አሸናፊ (የመልስ ጨዋታ በሜዳችን)

(ግብጽ በ1ኛው ዙር የምትገትመው የጅቡቲ እና ኮንጎ ጨዋታ አሸናፊን ሲሆን በ1ኛው ዙር የሚያሸንፈው ቡድን የኢትዮጵያ እና ካሜሩን አሸናፊን ይገጥማል፡፡)

ኢትዮጵያ በሁለቱ ዙሮች ተጋጣሚዎቿን በድር ውቴት ካሸነፈች ለመጀመር ጊዜ በተሳተፈችበት ማጣርያ ለጆርዳኑ የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ታልፋለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *