የፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ቅድመ ጨዋታ ዜናዎች

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከረጅም ጊዜ መቋረጥ በኋላ የ3ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ያስተግዳል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ከየክለቦቹ ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚደረጉ ጨዋታዎች የሚያመልጧቸው ተጫዋቾችን አጠናቅራ እንዲህ አሰናድታለች፡፡

 

ኤሌክትሪክ ቅዱስ ጊዮርጊስ

(ቅዳሜ ታህሳስ 2 በ10፡00 – አአ ስታድየም)

ከሁለት ጨዋታ 3 ነጥብ የያዘው ኤሌክትሪክ አምበሉ አልሳዲቅ አልማሂ እና ደረጄ ኃይሉን በጉዳት አያሰልፍም፡፡ ጊዮርጊስን ለቆ ኤሌክትሪክን የተቀላቀለው ፍፁም ገብረማርያም ነገ ለክለቡ የመጀመርያ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶስት ተጫዋቾችን ይዞ ወደ ሜዳ አይገባም፡፡ ሳላዲን በርጊቾ ፣ ራምኬል ሎክ እና አስቻለው ታመነ ከብሄራዊ ቡድን በጉዳት በመመለሳቸው አይጫወቱም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾቹን በጉዳት ቢያጣም የአምናው የፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች በኃይሉ አሰፋ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ወደ ሜዳ መመለሱ ለፈረሰኞቹ መልካም ዜና ነው፡፡ በ2006 ክለቡን ያሰለጠኑት ማርት ኑይም ለመጀመርያ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይመራሉ፡፡

 

ሀዋሳ ከነማ ከ ሀዲያ ሆሳእና

(ቅዳሜ ታህሳስ 2 በ9፡00 – ሀዋሳ)

ሁለቱንም ጨዋታ አቻ በመውጣት የጀመረው ሀዋሳ ከነማ አሁንም የአጥቂው ተመስገን ተክሌን ግልጋሎት አያገኝም፡፡ በውድድር ዘመኑ በጉዳት ምክንያት ምንም ጨዋታ ያላደረገው ተመስገን ከጉዳቱ ለማገገም ጊዜ ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡ ዘንድሮ ቡድኑን ተቀላቅሎ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኃይማኖት ወርቁ በልምምድ ጨዋታ በደረሰበት ጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ከሀዲያ ሆሳእና በኩል ምንም የተጫዋች ጉዳት የለም፡፡

 

ዳሽን ቢራ ከ ወላይታ ድቻ

(ቅዳሜ ታህሳስ 2 በ9፡00 – ጎንደር)

ሁለቱንም ጨዋታ አሸንፎ የውድድር ዘመኑን የጀመረው ዳሽን ቢራ ተክሉ ተስፋዬ ፣ ኪዳኔ ተስፋዬ እና ዮናስ ግርማይን በጉዳት አያሳለፍም፡፡ ከማሊ እና ጋና የመጡት ተጫዋቾችም ጉዳት አጋጥሟቸዋል፡፡

በወላይታ ድቻ በኩል ከዘላለም እያሱ በቀር ሁሉም ለጨዋታ ብቁ ሆነውለታል፡፡ ከደደቢት ጋር በተደረገው ጨዋታ ከባድ ጉዳት ያስተናገደው ዘላለም ምናልባትም ቀጣዮቹ 5 ጨዋታዎች ሊያመልጡት ይችላሉ፡፡

 

ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከነማ

(ቅዳሜ ታህሳስ 2 በ9፡00 – ይርጋለም)

ሲዳማ ቡና የመስመር አማካዩ እንዳለ ከበደን ወደ ሜዳ ይዞ እንደማይገባ ሲረጋገጥ በክረምቱ መኪና አደጋ ደርሶባቸው የነበሩት ዋና አሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራው በውድድር አመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ቡድናቸውን እየመሩ የነጥብ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡

ድሬዳዋ ከነማ አዲስ ፈራሚው ዳዊት እስጢፋኖስን ሳይዝ ሲዳማ ቡናን ይገጥማል፡፡ ዳዊት ለክለቡ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ መፈረሙ ቢረጋገጥም የወረቀት ጉዳዮች ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቃቸውና ከተሰለፈ ፎርፌ እንዳይሰጥባቸው በመስጋታቸው የዚህ ሳምንት ጨዋታ ያመልጠዋል ተብሏል፡፡ በቀጣዩ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ግን ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

አርባምንጭ ከነማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

(ቅዳሜ ታህሳስ 2 በ9፡00 – አርባምንጭ)

ከ2 ጨዋታ 3 ነጥብ የያዘው አርባምንች ከነማ ባንክን በሚገጥምበት ጨዋታ የአዲስ ፈራሚው ኤርሚያስን ፣ ዘንድሮ ቡድኑን የተቀላቀለው የቀድሞው ባንክ ተጫዋች አብይ በየነን እንዲሁም የግብ ጠባቂው መሳ አያኖን ግልጋሎት አያገኝም፡፡

ንግድ ባንክ በተቃራኒው ካለምንም ጉዳት በተሟላ ቡድን ወደ አርባምንጭ ተጉዟል፡፡

 

 ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ከነማ

(እሁድ ታህሳስ 3 በ9፡00 – አዲስ አበባ ስታድየም)

ኢትዮጵያ ቡና የሊጉ መሪ አዳማ ከነማን በሚያስተናግድበት ጨዋታ 5 ተጫዋቾችን ያጣል፡፡ ከወላይታ ድቻ ጋር በተደረገው የእርዳታ ማሰባሰብያ ጨዋታ ከባድ ጉዳት ያስተናገደው ግብ ጠባቂው ሀሪሰን ሀሶው የማይሰለፍ ሲሆን የመስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድ እና አጥቂው ያቡን ዊልያም በጉዳት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ መጠነኛ ጉዳት ያለባቸው አካሉ አበራ እና አማኑኤል ዮሃንስ ለጨዋታው የመድረሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡

ከ2 ጨዋታ 6 ነጥብ የሰበሰበው አዳማ ከነማ የአጥቂ አማካዩ ወንድሜነህ ዘሪሁን እና አምበሉ ሱሌይማን መሃመድን በጉዳት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚደረገው ጨዋታ አያሰልፍም፡፡

 

ደደቢት ከ መከላከያ

(እሁድ ታህሳስ 3 በ11፡00 – አአ ስታድየም)

3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደደቢት በብሄራዊ ቡድን ጨዋታ በብሽሽቱ ላይ ጉዳት የገጠመው ስዩም ተስፋዬን አያሰልፍም፡፡ ለደደቢት እንደ መልካም ዜና የሚታየው የተካልኝ ደጀኔ እና ዳዊት ፍቃዱ ከጉዳታቸው ሙሉ ለሙሉ አገግመው ልምምድ መጀመራቸው ነው፡፡

በገብረመድህን ኃይሌው ቡድን በኩል መሃመድ ናስር በጉዳት አይሰለፍም፡፡ አጥቂው በሴካፋ ጨዋታዎች ላይ ጉዳት ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡ ከ6 ወር በላይ በጉዳት ከሜዳ ርቆ የቆየው ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ግን ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን ምናልባትም የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ጨዋታ ሊያደርግ ይችላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *