ዛሬ በወጣው የ2016 የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል፡፡
የ2007 የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣርያው ከሳምንት በኋላ የሚጠናቀቀው የሲሸልስ ሊግ አሸናፊ ክለብ ጋር ይገናኛል፡፡
10 ክለቦችን የሚያሳትፈው የ2015 የሲሸልስ ሊግ ሊገባደድ የ2 ሳምንታት እድሜ ብቻ የቀረው ሲሆን ሴይንት ሚቼል በ35 ነጥቦች ይመራል፡፡ ሴይንት ሌዊስ ሰንስ ዩናይትድ በ33 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፎረስተርስ በ30 ነጥቦች ጠባብ የቻምፒዮንነት ተስፋን ሰንቆ ይከተላል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን ዙር ካለፈ ከ2015 የቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ቲፒ ማዜምቤ ጋር ይገናኛል፡፡ ዩሲኤም አልጀርን አሸንፎ ለ5ኛ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግን ክብር የተጎናፀፈው የኮንጎው ሃያል ክለብ 80ኛ አመቱን በማክበር ላይ ለሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፈረሰኞቹ ይህንን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ በሁለተኛው ዙር (ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት) ከሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ / የኒጀሩ ዶዋኔስ እና ከኬንያው ጎር ማሂያ/ የማዳጋስካሩ CNaPS Sport አሸናፊን ይገጥማሉ፡፡
የጥሎ ማለፉ አሸናፊ መከላከያ በመጀመርያ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታው የግብፅ ሊግን በ4ኛነት ካጠናቀቀው ሚስር ኤል-ማካሳ ጋር ይጫወታል፡፡
ጦሩ ቅድመ ማጣርያውን በአሸናፊነት ከተወጣ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ሌላውን የኮንጎ ክለብ ዶን ቦስኮ ይገጥማል፡፡ ዶንቦስኮን የሚያልፍ ከሆነ ደግሞ ወደ ምድ ድልድል ለመግባት የናሳራዋ ዩናይትድ (ናይጄርያ) / ጄኔሬሽን ፉት (ሴኔጋል) እና የአልጄርያው ኮንስታንቲኖስ አሸናፊ ጋር ይገናኛል፡፡
ሁለቱም ክለቦች የቅድመ ማጣርያውን የመጀመርያ ጨዋታ ከፌብሩወሪ 12-14 ባሉት ቀናት ሲያከናውኑ የመልሱን ጨዋታ ከፌብሩወሪ 26-28 / 2016 ባሉት ቀናት ውስጥ ያደርጋሉ፡፡