በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ዛሬ 5 ጨዋታዎች ተደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሲዳማ ፣ ሀዋሳ እና ወላይታ ድቻ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ 14 ግቦችም ከመረብ አርፈዋል፡፡
ሀዋሳ ላይ ሀዲያ ሆሳእናን ያስተናገደው ሀዋሳ ከነማ በመጨረሻ ሰአት በተቆጠረች ግብ 4-3 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ሀዲያዎች የውድድር ዘመናቸውን የመጀመርያ ድል ለማግኘት ሁለት ጊዜ የመምራት አጋጣሚ ቢያገኙም አልተጠቀሙበትም፡፡
የሀዋሳን የድል ግቦች ጋዲሳ መብራቴ (2) ፣ ፍርዳወቅ ሲሳይ እና አመለ ሚልኪያስ ሲያስቆጥሩ የሀዲያ ሆሳእናን ግቦች ዱላ ሙላቱ (2) እና አበባየሁ ዮሃንስ አስቆጥረዋል፡፡
አርባምንጭ ላይ ንግድ ባንክን ያስተናገደው አርባምንጭ ከነማ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡ አርባምንጭ በረከት ወ/ፃድቅ ባስቆጠረው ግብ 1-0 ቢመራም ኤፍሬም አሻሞ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሴኮንዶች ሲቀሩ እንግዶቹን አቻ የምታደርግ ግብ አስቆጥሯል፡፡
ድሬዳዋ ከነማን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 2-1 አሸንፎ የውድድር ዘመኑንየመጀመርያ ድል አሳክቷል፡፡ የሲዳማን የድል ግቦች አዲስ ፈራሚዎቹ በረከት አዲሱ እና ላኪ ባሪለዱም ሲያስቆጥሩ ይሁን እንደሻው የድሬዳዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ሲዳማ ቡና በሊጉ ድል ሲያስመዘግብ ከ8 ወራት (9 ጨዋታዎች) በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ወላይታ ድን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል፡፡ በዛብህ መለዮ ለእንግዶቹ ወሳኟን የማሸነፍያ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
በ11፡30 ኤሌክትሪክን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸንፏል፡፡ የፈረሰኞቹን ግብ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ያሳረፈው አሉላ ግርማ ነው፡፡ አሉላ ከማእዘን ምት የተሸገረችለትን ኳስ ከርቀት በቀጥታ በመምታት ያስቀጠራት ግብ ከተመልካቹ አድናቆት አስገኝታለታለች፡፡
የ3ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነገ ሲካሄዱ ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከነማን 9፡00 ላይ ያስተናግዳል፡፡ ከሁለቱ ጨዋታ በመቀጠል መከላከያ እና ደደቢት በ11፡30 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከነማ ፣ ወላይታ ድቻ እና ዳሽን ቢራ በእኩል 6 ግብ ሲመሩት ሀዋሳ ከነማ በ5 ነጥብ ይከተላል፡፡