ከሜዳ የራቀው ፋሲካ አስፋው አሁን ስላለበት ሁኔታ ይናገራል

ፋሲካ አስፋው በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከደደቢት ጋር ወደ መቐለ አብሮ ተጉዞ ከአስራ አምስት ቀናት በላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እየሰራ ቢቆይም በአንድም ጨዋታ ላይ ሳይሰለፍ ቀርቷል።

በአሁኑ ወቅት ክለብ አልባ የሆነው ፋሲካ ወቅታዊ ሁኔታውን በተመለከተ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው ቃል በግል ጉዳይ ምክንያት ከደደቢት ጋር እንደተለያየ ገልጿል። ” የት ነህ ብሎ አስቦ የደወለልኝ ሚዲያ የለም፤ አስባቹ በመደወላቹ አመሰግናለው። በአሁኑ ሰዓት እግርኳስን እየተጫወትኩ አይደለም። ይህ ግን እግርኳስን አቁሜያለው ማለት አይደለም። ዘንድሮ ደደቢት ነበርኩ፤ ዝግጅትም ከቡድኑ ጋር ለተወሰኑ ቀናት አብሬ ሰርቼ ነበር። ሆኖም የግል ጉዳይ አጋጥሞኝ ለደደቢት ሳልጫወት ወደ አዲስ አበባ መጥቼ አልተመለስኩም። ”

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ፋሲካ በቀጣይ ዓመት ወደ ሜዳ ለመመለሰ ማቀዱንም ተናግሯል። ” አንደኛው ዙር ሲጠናቀቅ ብዙ ክለቦች ደውለውልኝ እኔን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይተው ነበር። እኔ ደግሞ በዚህ ዓመት መጨረስ የሚገቡኝ አንዳንድ ጉዳዮች በመኖራቸው ፍቃደኛ አልሆንኩም። በቀጣይ ዓመት ግን ወደምወደው እግርኳስ እመለሳለው ብዬ አስባለሁ። ምንም አይነት እግርኳስን የማቆብ ሀሳብ የለኝም፤ ለመጫወት የሚከለክለኝ ጉዳትም የለብኝም ” ብሏል።

እልኸኛ እና ለካርዶች ቅርብ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል የሚመደበው “መሳይ” በ1990ዎቹ አጋማሽ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቡና ዋና አሰልጣኝ በነበረው ካሳዬ አራጌ አማካኝነት ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ለሁለት ዓመት ቆይቶ ጎልቶ ወደወጣበት እና ምርጥ አቋሙን ወዳሳየበት መከላከያ በማምራት ለስድስት ዓመታት ቆይታ ካደረገ በኋላ በ2004 በድጋሚ ወደ አሳዳጊ ክለቡ በመመለስ ኢትዮጵያ ቡናን ማገልገል ችሏል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቶ ያሳለፈው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ በግሉ የመጀመርያ የሆነውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ባነሳበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጫወተ በኋላ ወደ አዳማ ከተማ በማቅናት እስከ 2009 ድረስ ተጫውቶ ወደ ደደቢት አምርቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡