ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ደደቢት

በነገው ዕለት ከሚደረጉት ስምንት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን የትግራይ ክለቦች የሚያገናኘውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በዚህ ሳምንት በትግራይ ስታድየም የሚደረገው ብቸኛ መርሐ ግብር ሁለት ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖች የሚገናኙበት እንደ መሆኑ ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። ከተከታታይ መልካም ብቃት በኃላ ባለፈው ሳምንት በረመዳን ናስር የተጨማሪ ሰዓት ግብ ከድሬዳዋ በሽንፈት የተመለሱት ወልዋሎዎች ነገም እንደ ባለፉት ጨዋታዎች በመስመር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ሲጠበቅ ተጋጣሚያቸው ደደቢት ለመስመር ጥቃት የግራ እና ቀኝ አማካዮቻቸውን ከጥልቀት እንዲነሱ እና መከላከሉ ላይ እገዛ እንዲያደርጉ የሚደርግ ቡድን የያዙ እንደመሆኑ ወልዋሎዎች የሚያጠቁበት መንገድ ላይ መጠነኛ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ወልዋሎዎች ባለፉት ጨዋታዎች ጥሩ ብቃት ላይ የነበረው አማካያቸው አማኑኤል ጎበና በጉዳት ስላጡ ከረጅም ግዜ ጉዳት በኃላ ወደ ጨዋታ የተመለሰው ኤፍሬም ኃይለማርያም እና ብርሃኑ አሻሞ በአማካይ መስመር ላይ ያጣምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለተኛው ዙር በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ጀምረው ተከታታይ ሽንፈት የገጠማቸው ደደቢቶች ከወዲሁ ከሊጉ መውረዳቸው ላለማረጋገጥ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ብቸኛ አማራጫቸው ነው። ባለፉት ጨዋታዎች ጋናዊው አጥቂያቸው በቅጣት በማጣቸው የሚያጠቁበት መንገድ ወደ 4-4-2 የቀረበ አጨዋወት በመቀየር ሁለት ጨዋታዎች ያደረጉት ሰማያዊዎቹ በዚህ ጨዋታም ጋናዊውን አጥቂ ፉሰይኒ ኑሁን በቅጣት ስለማያገኙ አጨዋወታቸው ላይ ለውጥ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። ከዚህ በተጨማሪ 4-2-3-1ን መርጠው ባደረግዋቸው ጨዋታዎች ከሶስቱ አማካዮች ሁለቱ እንዳለ ከበደ እና መድኃኔ ብርሃኔ አማካኝነት በመስመር የሚደረገው ጥቃት ለመመከት የተሻለ ቅርፅ የተላበሱት ደደቢቶች የነገው ተጋጣምያቸው በመስመር የሚያጠቃ ቡድን እንደመሆኑ ከሁለት ጨዋታ በኋላ አሰላለፋቸውን ወደ 4-4-2 ይመልሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። አቤል እንዳለ ከግል ጉዳይ በመመለሱ የአብስራ ተስፋዬ ፣ ዓለምአንተ ካሳ እና አቤል እንዳለ ድንቅ የአማካይ ክፍል ጥምረት ያገኙት ደደቢቶች ከመስመር አጨዋወታቸው በተጨማሪ መሃል ለመሃል የሚደረግ ጥቃት ሁለተኛ አማራጫቸው አድርገው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ደደቢቶች በዚህ ጨዋታ ኑሁ ፉሴይኒ በቅጣት የማያገኙ ሲሆን ሌላ የሚያጣው ተጫዋቾች ግን አይኖርም።

በእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ወደ ሊጉ በመጣበት የአምናው የውድድር ዓመት ጅምሮ ቡድኖቹ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው ወልዋሎ ሁለት ጊዜ በ1-0 ውጤት ሲያሸንፍ ደደቢት ደግሞ አንድ ጊዜ የ3-1 ድል ቀንቶታል።

– የትግራይ ስታድየምን በጋራ እየተጠቀሙ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች እዛው ሜዳ ላይ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ደደቢት ሦስት ሽንፈቶችን ሲያስተናግድ ወልዋሎ ደግሞ ከሦስት ጨዋታዎች በአንድ ድል እና በአንድ አቻ ውጤት አራት ነጥቦችን አሳክቷል።

ዳኛ

– እስካሁን በዳኘባቸው ሦስት ጨዋታዎች 14 የመጀመሪያ እንዲሁም አንድ ሁለተኛ የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶችን የመዘዘው ዳንኤል ግርማይ ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነትን ወስዷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ/ዩ (4-2-3-1)

ዓብዱልአዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – በረከት አማረ – ደስታ ደሙ – ብርሃኑ ቦጋለ

ኤፍሬም ኃይለማርያም – ብርሃኑ አሻሞ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – አፈወርቅ ኃይሉ – ኤፍሬም አሻሞ

ሬችሞንድ አዶንጎ

ደደቢት (4-2-3-1)

ሙሴ ዮሃንስ

ዳግማዊ አባይ – አንቶንዮ አቡዋላ – ኃይሉ ገብረ የሱስ – ሄኖክ ማርሹ

አቤል እንዳለ – የአብስራ ተስፋዬ

መድኃኔ ብርሀኔ – አለምዓንተ ካሳ – እንዳለ ከበደ

መድሀኔ ታደሰ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡