ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ሲዳማ ቡና

ከ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ጅማ እና ሲዳማ የሚገናኙበትን ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን ለመመልከት አስቀድመነዋል።

በሦስት ነጥቦች ልዩነት 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲዳማ እና አባ ጅፋር ነገ 09፡00 ላይ በጅማ ስታድየም ይገናኛሉ። በሁለተኛው ዙር ጥሩ መሻሻልን እያሳየ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ሽረ እና ደደቢት ላይ ባሳካው ተከታታይ ድል ታግዞ በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ወዳለው ፉክክር መቅረብ ችሏል። ከሜዳቸው ውጪ ባላቸው ደካማ ሪከርድ የቀጠሉት ሲዳማዎች ደግሞ በፉክክሩ የነበራቸው ፍጥነት ቀንሶ ሁለተኝነቱን ለፋሲል በማስረከብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሜዳቸው ላይ ሽንፈት ካላገኛቸው ቡድኖች መካከል የሚገኙት ጅማዎች በነገውም ጨዋታ ነጥባቸውን ከተጋጣሚያቸው ጋር በማስተካከል መሪውን ለመቅረብ ሲጫወቱ ሲዳማዎችም ሁለተኛ ደረጃን ዳግም ለማግኘት እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

በጨዋታው ጅማ አባ ጅፋሮች ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄዬ በግል ጉዳይ ወደ ጋና በማቅናቱ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆንባቸው አምበሉ ኤልያስ አታሮም በዛሬው ልምምድ ላይ በህመም ምክንያት አቋርጦ በመውጣቱ ወደ መጀመሪያው አሰላለፍ ውስጥ መካተቱ አጠራጣሪ ሆኗል። በአንፃሩ ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳት ከቡድኑ ጋር ያልነበሩት መስዑድ መሀመድ እና አስቻለው ግርማ ከጉዳታቸው ሙሉ ለሙሉ በማገገማቸው ለጨዋታው ብቁ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። የሁለቱ ተጫዋቾች መመለስ ቡድኑ በቅርብ ጨዋታዎች መከተል በጀመረው የ4-4-2 አሰላለፍ ውስጥ አማራጮችን እንደሚሰጠው ይጠበቃል። በዋነኝነትም ወደ መሀል አጥብበው ከሚጫወቱት የመስመር አማካዮቹ ወደ ፊት በሚላኩ ኳሶች ላይ ተመስርቶ በኦኪኪ አፎላቢ እና ማማዱ ሲዲቤ ጥምረት አማካይነት ተደጋጋሚ ለውጦች የሚደረጉበት እና ጫና ውስጥ ሲገባ የሚታየውን የሲዳማ የኋላ ክፍል እንደሚፈትኑ ይጠበቃል።

ወሳኝ አጥቂያቸው አዲስ ግደይ በሽረው ጨዋታ ግብ ወደ ማስቆጠሩ የተመለሰለት ሲዳማ ቡና በዋነኝነት የባለሜዳዎቹን ጥቃት በመግታት ላይ አተኩሮ ወደ መስመር አጥቂዎቹ በሚላኩ ቀጥተኛ ኳሶች ከመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክር ይጠበቃል። በተጋጣሚዎች የአማካይ ክፍል ሲዋጥ የሚታየው የቡድኑ የመሀል የሦስትዮሽ ጥምረት ከመስመር አጥቂዎቹ ድጋፍ እንደሚያገኝ በሚጠበቅበት ጨዋታ ቡድኑ መሀመድ ናስርን በህመም እና ወንድሜነህ አይናለምን ደግሞ በጉዳት ማጣቱ ለቀጥተኛ አጨዋወት ምቹ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል። ከሁለቱ በተጨማሪም ሲዳማ ቡና ከጉዳት መሳይ አያኖ እና ዮናታን ፍሰሀን በጉዳት ወደ ጅማ ይዞ ያልተጓዘ ሲሆን ግሩም አሰፋ ደግሞ ከጉዳት ይመለስለታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ እስካሁን በሊጉ ሦስት ጊዜ ሲገናኙ ቻምፒዮኖቹ ወደ ሊጉ ባደጉበት የ2010 የውድድር ዓመት ሁለተኛ ዙር ከሜዳቸው ውጪ 3-1 ካሸነፉበት ጨዋታ ውጪ ሁለት ጊዜ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

– ጅማዎች በሜዳቸው አስር ጨዋታዎችን ሲያደርጉ አንዴም ሽንፈት ሳያገኛቸው የቀጠሉ ሲሆን ግማሹን በድል ግማሹን ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። ባለፉት ስድስት የሜዳ ላይ ጨዋታቸውም መረባቸውን አላስደፈሩም።

– ሲዳማ ቡና ከድቻ ጋር በገለልተኛ ሜዳ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ሳይጨምር ከሜዳው ውጪ ስምንት ጨዋታዎችን ያከናወነ ሲሆን ድል የቀናው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በተረፈ ሦስቴ ነጥብ ሲጋራ አራት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ጨዋታው አባ ጅፋር ከድሬዳዋ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ደግሞ ከድቻ የተገናኙበትን ጨዋታ በዳኘው በኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ መሪነት ይከናወናል። አርቢትሩ እስካሁን በአስር ጨዋታዎች 38 የቢጫ ካርዶችን ሲመዝ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባጅፋር (4-4-2)

ዘሪሁን ታደለ

ዐወት ገ/ሚካኤል – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ተስፋዬ መላኩ

ዲዲዬ ለብሪ – መስዑድ መሀመድ –ይሁን እንዳሻው – አስቻለው ግርማ

ኦኪኪ አፎላቢ – ማማዱ ሲዲቤ

ሲዳማ ቡና ( 4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ዳግም ንጉሴ

ዳዊት ተፈራ –ዮሴፍ ዮሃንስ – ግርማ በቀለ

ይገዙ ቦጋለ – ሐብታሙ ገዛኸኝ – አዲስ ግደይ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡