ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ ኤምሲ አልጀር ኤምኦ ቤጃን 1-0 በስታደ 5 ጁሌት 1962 ላይ ባሸነፈበት ጨዋታ ቋሚ ሆኖ ተሰልፏል፡፡ ሳላ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ያሳየው ጥሩ አቋም ወደ አልጀርሱ ክለብ ቋሚ 11 ውስጥ እንዲገባ አስችሎታል፡፡
የኤምሲ አልጀርን የድል ግብ አብደራህማን ሃቾድ በ78 ደቂቃ በተሰጠ የፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ ድሉን ተከትሎ ኤምሲ አልጀር በ22 ነጥብ 3ተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡
የአልጄሪያ ሊግ 1ን የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረው ሁኤስም አልጀር በ32 ነጥብ ይመራል፡፡
ጌታነህ ከበደ ክለቡ ዩንቨርሲቲ ኦፍ ፒሪቶሪያ ከሜዳው ውጪ በጎብል ፓርክ ከፍሪ ስቴት ስታርስ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ በ46ኛው ደቂቃ ላኪ ማቶሲን ቀይሮ በመግባት መጨወት ችሏል፡፡
1-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በዳኒ ቬንተር የ37ኛ ደቂቃ ግብ ሲመሩ ቢቆዩም አማተክሶች በ58ኛው ደቂቃ በሌኔክስ ባሴላ አማካኝነት አቻ የምታደርጋቸውን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ለግቧ መገኘት የጌታነህ ሚና ቁልፍ ነበር፡፡
ከቤድቬስት ዊትስ በውሰት ለአማተክስ የሚጫወተው ጌታነህ ግብ የማስቆጠር ዕድል ቢያገኝም የፍሪ ስቴት ስታሩ ግብ ጠባቂ ዳውዳ ዲያኬቴ አማክኗታል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ አማተክሶች በ6 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካን አብሳ ፕሪምየር ሺፕ ቤድቬስት ዊትስ በ26 ነጥቦች ይመራል፡፡
ፍቅሩ ተፈራ ተቀይሮ በገባበት የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ቼኔይን የዓምና ሻምፒዮኑን አትሌቲኮ ኮልካታን 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡
በደቡብ ህንድ ቼኔይን ባለው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ፑኔ ላይ በተካሄደው ወሳኝ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪ ዙር ጨዋታ ባለሜዳው ቼኔይን ሙሉ ብልጫ ተንፀባርቋል፡፡
በ79ኛው ደቂቃ የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የሚመራውን ኮሎምቢያዊው ሲቲቨን ሜንዶዛ ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፍቅሩ የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡ የቼኔይን ሶስት ግቦች ብሩኖ ፔሊሳሪ በ38ኛው ደቂቃ፣ ጄጄ ላፔክሁላ በ57ኛው ደቂቃ እንዲሁም ስቲቨን ሜንዶዛ በ68ኛው ደቂቃ አስመዝግቧል፡፡
በቱርክ ስፖር ቶቶ ሱፐር ሊግ የሚወዳደረው የዋሊድ አታው ገንሰልበርሊጊ በሜዳውን እና በደጋፊው ፊት በሲቫስፖር 1-0 ተረትቷል፡፡ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ጆን ቦይ በ24ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡
ዋሊድ በቡድኑ ውስጥ ባለመካተቱ ጨዋታው አምልጦታል፡፡ ገንሰልበርሊጊ በ13 ነጥብ እና በስምንት የግብ ዕዳ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቤክሺታሽ በ32 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ለመቀመጥ ችሏል፡፡